ሕወሓት የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ይገምገም ሲል አፍሪካ ሕብረትን ጠየቀ

በምርጫ ቦርድ ሕጋዊነቱ የተሰረዘበት ሕወሃት፣ የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አደራዳሪ አካል የስምምነቱን አተገባበር እና የሌላ ዙር ጦርነት ስጋትን ለመገምገም በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ጥሪ አቀረበ። የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከኅዳር 8 እስከ 13 ያካሄደውን ስብሰባ ማጠናቀቁን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ አፍሪካ ኅብረት እና ስምምነቱ እንዲፈረም አስተዋጽኦ ያደረጉ አገራት እና ዓለማቀፍ ድርጅቶች ስምምነቱ ከምንጊዜውም በበለጠ አደጋ ላይ መውደቁን እንዲገነዘቡ አሳስቧል። ፌደራል መንግስቱ የታጠቁ ቡድኖችን በማደራጀት እና በማስታጠቅ የግጭት ማቆም ስምምነቱን ጥሷል በማለት የከሰሰው የሕወሃት መግለጫ፣ መንግሥት ተጨማሪ ጥፋት ከሚያስከትል ሌላ ዙር ጦርነት እንዲቆጠብ፣ በግጭት ማቆም ስምምነቱ መሰረት ግዴታውን ለመወጣት ከሕወሃት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር እንዲሰራ እና የትግራይን ሕዝብ በርሃብ ለማጥቃት እና ወደ አመጽ ለመግፋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ሕወሃት ማሳሰብ ይፈልጋል ብሏል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በትግራይ ኃይሎች ላይ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት “በከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ” የተፈጸመ መሆኑን ያመለክታል በማለትም ሕወሃት መንግሥትን ከሷል።