አማራን የሚወክሉ ጭንቅላቶች በእስር ቤት ውሰጥ ታጉረው የሚደረግ አገራዊ ምክክር ወደፊትም ቢሆን ጥያቄ እንደሚያስነሳ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለማራዘም ዛሬ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ዛሬም እንደተለመደው የሕዝብን ጥያቄ ለኮሚሽኑ አባሎች አቅርበዋል።
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ሕዝቡ መሪዎቼ ብሎ የሚጠራቸው የአማራ ልሂቃን ማለትም ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች እንዲሁም የሕዝብ እንደራሴዎች በፖለቲካ አስተሳሰባቸውና አማራ በመሆናቸው ብቻ አስር ቤት ባሉበት ሁኔታ የሚደረግ ሀገራዊ ምክክር ነገም ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል።
የፓርላማ አባሉ አክለውም እነዚህን በእስር ላይ የሚገኙ የአማራ ጭንቅላቶችን ለማስፈታት የምታደርጉትን እንቅስቃሴ መንግስት ካልተቀበለው ለሕዝቡ ማቅረብ አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
በነገራችን ላይ ሌሎች ህዝቦች የታሰረ ሊህቃን የላቸውም ለምሳሌ ከትግራይ የታሰረ የፖለቲከኛ ሊህቃን የለም፣ ከኦሮሞም ብዙ የተሰሩ ነበሩ ተፈተዋል ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ጨምረውም በሰፊው ታስሮ ያሉ ሊህቃኖች ከአማራ ህዝብ ያሉ ተወካዮች ብቻ ናቸው፤ ስለዚህ ነገ የአማራ ህዝብ ሊህቃኖቸ ታስረውብኛል አልተወከልኩም ቢል በቂ ምክንያት አለው ብየ አስባለሁ። እነማን ምን ሲያደርጉ እንደታሰሩ እና እንደተፈቱ እናውቃለን በዚሁ ሀገር ብለዋል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ
የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽንም እኛ አክቲቪስት አይደለንም መንግስት እንቢ አለን ብለን ወጥተን የምንናገረው ሲሉ ተሳልቀዋል።
በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና ሰቆቃ ወጥተው በማጋለጣቸውና በመሞገታቸው ብቻ በርካታ የአማራ ጭንቅላቶች በእስር ቤት ይገኛሉ።
ላለፉት ሶስት አመታት ያለ ፍርድ እስር ቤት ታጉረው የሚገኙት እነዚህ የአማራ ሊሂቃን አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሲፒጄን ጨምሮ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ቢያሳስቡም አገዛዙ ግን አሁንም በእስር ቤት እያሰቃያቸው ይገኛል።
የሕዝብ ተመራጮቹ ዮሐንስ ቧያለው፣ ክርስቲያን ታደለና ካሳ ተሻገር፣ ጋዜጠኞቹ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ መስከረም አበራና ዓባይ ዘውዱን ጨምሮ ለአማራ ሕዝብ ጥቅሞች የተከራከሩ ከ200 በላይ የፖለቲካ እስረኞች በ 57 ፖለቲካዊ የክስ መዝገቦች ተከሰዋል።