ኬንያ፣ “ሊናካፓቪር” የተሠኘውን አዲሱን የኤች አይ ቪ መከላከያ መድሃኒት በመረከብ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር ኾነች። መድሃኒቱ፣ ቫይረሱ የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱ እንዳይተላለፍባቸው መከላከል የሚችል ሲኾን፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚሠጥ ነው። ኬንያ፣ መድሃኒቱን በቀጣዩ ወር መስጠት እንደምትጀምር ተገልጧል። መድሃኒቱ በዓመት ላንድ ሰው 60 ዶላር የሚወጣበት ሲሆን፣ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የመከላከል እድሉ 99 ነጥብ 9 በመቶ እንደሆነ ተነግሮለታል። አዲሱን የኤች አይ ቪ መከላከያ መድሃኒት እንዲረከቡ ግሎባል ፈንድ እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የኤች አይ ቪ ፕሮግራም ከመረጧቸው የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ የአፍሪካ አገራት አንዷ ኬንያ ስትሆን፣ ሌሎቹ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ እስዋቲኒ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጀሪያ፣ ሌሶቶ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ናቸው።