ከአፋብን ምኒልክ ዕዝ የጤና መምሪያ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ፍፁም ሰብአዊ በሆነው የጤና ሙያ ውስጥ የምትገኙ ወንድሞቻችን/እህቶቻችን ኑ ተጋግዘን ኢ-ሰብአዊ የሆነውን ሥርአት እንቀይር!
አማራ ተኮር የሆነው የዘር ማጥፋት ጦርነት በተለየ መልኩ በይፋ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ የጤና ተቋማት፣ የጤና ሙያተኞች እና የጤና አገልግሎት የፋሽስታዊዩ ሥርአት አይነተኛ ኢላማዎች በመሆናቸው ሥርአቱ ህክምና መከልከልን እንደጦር መሣሪያ እንደሚጠቀም ግልፅ ማስረጃዎች ናቸው። ሥርአቱ ጤና ተቋማትና ግብአቶቻቸው ላይ የሚፈፅመው የጦርና የሠብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች አለም ያወቃቸውና ፀሐይ የሞቃቸው ጉዳዮች በመሆናቸው እነኚህን ጉዳዮች አሁን ላይ ደግሞ መናገር ለአብዛኞቻችሁ ለቀባሪ መርዶ እንደመናገር እንደሚሆን አያጠያይቅም።
ዘይግይቶም ቢሆን ግን የአለም ጤና ድርጅትም ሳይቀር የህዝባችንን የህልውና ችግርና የጤና አገልግሎቱ የገጠመውን ሥርአት መር ፈተና መረዳቱን በዋና ዳይሬክተሩ በኩል የዶ/ር ፀጋሁን ስሜን የግፍ ግድያን ተከትሎ በመግለፁ ሥርአቱ የሞት ጣር ላይ መድረሱን በግልፅ አመላክቷል። በዚህ አጋጣሚ ዶ/ር ፀጋሁንን የመሠለ የህክምና ዶክተር ለማፍራት በትንሹ ሩብ ክፍለዘመን የሚጠይቅ መሆኑን እንድታውቁት እና በህዝባችን ላይ ምን ያክል ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የዘር ማጥፋት እንደሚፈፀም እንድትረዱት አንፈልጋለን። ለዶ/ር ፀጋሁን ቤተሠቦችና ወዳጆች ሁሉ መፅናናትን እንመኛለን።
ጥያቄው ይህ ዘግናኝ ወንጀል እስከመቼ እና ስንት ሙያተኞቻችን እስከሚያልቁ ቁጭ ብለን እንመለከታለን? ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረው እና መንግስትን ተክቶ አገር የመምራት ቁመና ላይ የሚገኘው ድርጅታችን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄም ይሁን ዕዛችን የጤና ሙያተኞቻችን ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙ የአሸባሪው ስርአት አባላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ወይም በአለም አደባባይ ለፍርድ እንዲያቀርብልን የምኒልክ ዕዝ ጤና መምሪያ አበክሮ ይጠይቃል።
በመጨረሻም ምንም አይነት ከለላ ሊሠጣችሁ የሚችል ሀይልም ይሁን ሥርአት በሌለበት በአሸባሪው መንግስት ቀጠና ውስጥ ሆናችሁ ይህን ሁሉ ግፍና መከራ የምትቀበሉ የሙያ ጓዶቻችን ኑ ተጋግዘን ይህን አስከፊ ሥርአት በጋራ እንቀይር እያለ የምኒልክ ዕዝ ጤና መምሪያ የተለመደ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።