የግንብ አጥር ተደርምሶ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሰባት ሰዎች ህይወት አለፈ

የግንብ አጥር ተደርምሶ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሰባት ሰዎች ህይወት አለፈ

በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ በደረሰ የግንብ አጥር መደርመስ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የመቱ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራና ፍትህ አሰጣጥ ሥራ ሂደት መሪ ኮማንደር ተሾመ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው ትላንት ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ የደረሰው በከተማው ቀበሌ 01 ውስጥ ነው፡፡

የሰዎቹ ሕይወት ሊያልፍ የቻለው በከፍታ ተሰርቶ የነበረው አንድ የንግድ ድርጅት የግንብ አጥር በጎረቤት መኖሪያ ቤት ላይ ድንገት በመደርመሱ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በአደጋው በእንቅልፍ ላይ የነበሩ እናትና ስድስት ልጆቻቸው ሕይወት ወዲያውኑ ማለፉን ኮማንደር ተሾመ ተናግረዋል፡፡

ሕይወታቸውን ካጡ የቤተሰቡ አባላት አምስቱ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ህጻናት ናቸው፡፡

ኮማንደር ተሾመ እንዳሉት የድርጅቱ ባለቤት በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የአደጋው መንስኤም በመጣራት ላይ ነው፡፡

የሟቾቹ ጎረቤቶች እንደተናገሩት የቤተሰቡ አባላት በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡

በከተማው የቀን ሥራ እየሰራ ቤተሰቦቹን ሲያስተዳድር የነበረው የቤቱ አባወራን ከዓመት በፊት በሕመም ምክንያት ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል ፡፡