“የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅና አንድ አብሯቸው የነበረ አገልጋይ ተገድለዋል፤ በትክክል ግድያው እንደተፈጸመ አረጋግጠናል” – ቤተክርስቲያኗ

“የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅና አንድ አብሯቸው የነበረ አገልጋይ ተገድለዋል፤ በትክክል ግድያው እንደተፈጸመ አረጋግጠናል” – ቤተክርስቲያኗ

“ምዕመናን የተረጋጋ ኑሮ እየቀጠሉ አይደለም በቦታው፣ አገልጋዩም ይሄ ይከተለኛል ብሎ ከአገልግሎቱ ተቆጥቦ ነው ያለው!”

የሆሮጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ኤዶም ቀሲስ ድጉማ እና ቀሲስ ደሳለኝ ነሞምሳ የተባሉ አገልጋይ በታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸች። በቤተክርስቲያኗ በኃላፊነት ደረጃ የሚገኙ አካል፣ “ሰሞኑን የህዳር ፅዮን በዓል አክብረው ሲመለሱ የነበሩ የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅና ሌላ አገልጋይ፣ ሌሎችም በአጠቃላይ አምስት ሰዎች ታግተው ነበር። ሁለቱ ተገድለዋል” ብለዋል። “በትክክል ግድያው እንደተፈጸመ አረጋግጠናል። ሌሎቹን ግን እንደለቀቋቸው ነው የደረሰን መረጃ የሚመላክተው፤ ገዳዮቹ ህገወጥ ታጣቂዎች ናቸው” ያሉት እኚሁ አካል፣ “በአካባቢው ግን አብረዋቸው የሄዱ በርካታ ወጣቶች ነበሩ ወደ አረቶ ማርያም” ሲሉም ገልጸዋል። “ከአረቶ ማርያም ሲመለሱ ነው ሻምቦ አካባቢ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው በህገወጥ ታጣቂዎች የታገቱት። ከብዙ ጥረት በኋላ ሌሎቹን ሲለቋቸው ሁለቱ ግን እንደተገደሉ ነው መረጃው ያለን” ሲሉም ሟቾቹ መጀመሪያ ታግተው እንደነበር አስረድተዋል።

ስጋት እንዳላቸው ገልጸውላችሁ ነበር? አካባቢው ምን የተለየ ነገር አለ? ስንል የጠየቅናቸው የቤተክርስቲያኗን አመራር ምን መለሱ ? “በአካባቢው የክርስቲያኖች መገደል እና ሞት አዲስ አይደለም። ለረጅም ጊዜ በርካታ ምዕመናን እና አገልጋዮች ህይወታቸው አልፏል። ባለፈው አንድ አመታት ከስድስት ወራት ግን ምዕራብም ምስራቅ ወለጋም ላይ ቆም ብሎ ነበር። አሁን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የቤተክርስቲያን አባቶችን፣ ትልልቅ ኃላፊነት የተሰጣቸውን አገልጋዮችን በእንዲህ አይነት መልኩ ማጥቃት በጣም ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ የሚከትና አገልጋዩንም ሆነ አማኙን አንገት ያስደፋ አሳዛኝ ክስተት እየተፈጸመ ነው። የኃላፊ፣ የካህናትም የምዕመናን ነፍስ፣ ነፍስ ነፍስ ነው። በተለየ መልኩ እነዚህን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አገልጋዮች ጠብቆ እንዲህ አይነት እርምጃ መውሰዱ መልኩን ቀየር ያደርገዋል። የአካባቢው ታጣቂዎች ናቸው አጥቂዎቹ፤ ይሄ ነው ለማለት የሚያስችል ሁኔታም አይደለም። ብቻ ህገወጥ ታጣቂዎች ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እጅግ አዝነናል፣ ጉዳዩንም ከምስራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ጋር እየተነጋገርን ነው፣ ከሆሮ ጉድሩ ሻምቦ ወለጋ። ሁለቱ ምስራቅ ወለጋም ሆሮ ጉዱሩ ሻምቦንም የብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ናቸው። ጉዳዩን በሪፓርት መልክ ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረግን ነው” ብለዋል። ባለፉት አመታት ምን ያክል ምዕመናን ተገድለዋል ? ለሚለው ጥያቄ፣ ” ጥናት ይጠይቃል፤ ምክንያቱም መረጃ የመለዋወጥ እድሉ በጣም የጠበበ ነው፤ የኔትወርክ መቋረጥ፣ አገልጋዮች በፍርሃት ውስጥ መሆን የዶክመንት ልውውጣችን ምቹ አለመሆን ” ሲሉ መልሰዋል። ” በጥቅሉ ብዙ ምዕመናን ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ብዙ አገልጋዮችም ከሞት ባሻገር በመሰደድ፣ ላልተረጋጋ ኑሮ ተዳርገዋል፣ የሆነው ሆኖ ግን ይሄን ያህል ቁጥር ነው ብሎ ለመግለጽ የተጨበጠ የተሰነደ መረጃ ማቅረብ ይጠበቃል፣ ግን ምዕመናን የተረጋጋ ኑሮ እየቀጠሉ አይደለም በቦታው፣ አገልጋዩም ይሄ ይከተለኛል ብሎ ከአገልግሎቱ ተቆጥቦ ነው ያለው፣ እና በመንግስትም በኩል ልዩ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ይመስለኛል ” ሲሉም አክለዋል። ” የምዕመንና አማኞች ግድያ፣ እገታ መፈናቀል ተስፋፍቷል ፤ ቤተክርስቲያኗ ምን ጥረት አደረገች ? ጫና ማድረግ አለባት ” የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፤ ቤተክርስያኗ እንዲህ አይነት ጥቃት እንዲቆም ምን እያደረገች ነው ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለአመራሩ አቅርቧል።

የቤተክርስቲያኗ አመራር ምን መለሱ ? ” ችግሩ እንደሀገር ያለነው፤ እንዲህ አይነት ነገሮች የጋራ ምክክር፣ ጥረት ይጠይቃሉ። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞቿን የእግዚአብሔር ቃል ከማስተማር ውጭ ምንም ለማድረግ አትመርጥም። ለዜጎች ዋስትና መስጠት ያለበት መንግስት ነው በየትኛውም መልክ። ቤተክርስቲያን ተልኮዋ ሰውን በእግዚአብሔር ቃል ኮትኩታ አሳድጋ የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾች ማድረግ፤ ቤተክርስቲያን እንዲያገለግሉ በበጎ ምግባር ላይ እንዲጸኑ ማድረግ እንጂ ከእግዚአብሔርና ከጸሎች ውጭ ጥቃቱን የምትከላከልበት አቅም የላትም። ያሉትን ችግሮች ለመንግስት አቀረብንም አላቀረብን፣ መንግስት ዓይኑ ትልቅ ነው፤ ጆሮውም በሰፊው ይሰማል። የሆነው ሆኖ ግን በአማኝና አገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን  ጥቃት በመዋቅራችን በየጊዜው መረጃዎች ያውም በሚስተግር መንገድ ተቀብለን ለሲኖዶስ እናቀርባለን፣ ሲኖዶሱ ለመንግስት አካል ያቀርባል ” ብለዋል።