ደቡብ አፍሪካ 14 ኢትዮጵያውያን ዜጎች ወደ ሃገሯ ሊገቡ ሲሉ በኤርፖርት መያዟን አስታውቃለች።
የደቡብ አፍሪካ የድንበር አስተዳደር ባለስልጣን 5 ወንድና 9 ሴት ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ወደ “OR Tambo” አለም አቀፍ ኤርፖርት ቢደርሱም የመጡበት መንገድ አጠራጣሪ ሆኖ ስላገኘው ለተጨማሪ ምርመራ እንደያዛቸው ገልጿል።
አስተዳደሩ የኢትዮጵያውያኑ ጉዞ ከሰዎች ዝውውር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ያለ ሲሆን በተደረገ የመጀመሪያ ምርመራ ሰዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመልሰው በህገወጥ መንገድ ከመግባታቸው በፊት ወደ ሌሎች ጎረቤት ሃገራት ለመሻገር የተደረገ ጥረት እንደሆነ ገልጿል።
አስተዳደሩ በመንገደኞቹ የጉዞ መረጃ ላይ አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮችን ስላገኘ በኤርፖርት ተለይተው ለምርመራ መወሰዳቸውን አንስቷል።
የደቡብ አፍሪካ የድንበር አስተዳደር በሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ወደ ሃገሩ በተጭበረበረ ቪዛ ሊገቡ የነበሩ 16 የባንግላዴሽ ዜጎችንም ይዣለሁ ብሏል። ደቡብ አፍሪካ በእነዚህ 30 ሰዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራ መጀመሯን የገለፀች ሲሆን የሰዎችን ዝውውር ለመቆጣጠር የደህንነት እርምጃዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፃለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእያንዳንዱ መንገደኛ የ890 ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል።
ደቡብ አፍሪካ በሁለት በረራዎች ወደ ሃገሯ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓጓዙ 14 ኢትዮጵያውያንን እና 16 የባንግላዴሽ ዜጎችን ከሰዎች ዝውውርና የተሳሳተ ቪዛ ጋር በተያያዘ ከያዘች በኋላ መንገደኞቹን ባጓጓዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ቅጣት መጣሏን የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞቹን ሰነድ በተገቢ መልከ ሳያጣራ ወይም በአጠራጣሪ ሁኔታ ስር በማጓጓዙ በእያንዳንዱ መንገደኛ 890 ዶላር ወይም 15,000 የደቡብ አፍሪካ ራንድ እንዲከፍል ተቀጥቷል።
ደቡብ አፍሪካ የያዘቻቸው 30 ሰዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገች መሆኗን እና አሻራቸውን እየወሰደች መሆኗን ገልፃለች።
ደቡብ አፍሪካ የምርመራው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉም ሰዎች ወደመጡበት ሃገር ይመለሳሉ ያለች ሲሆን ሰዎቹንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደመጡበት እንዲመልስ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪነት አዛለች።