” ልጃችን መንገድ ላይ ተገድላ ከ600 ሺህ ብር በላይ ተወስዶባታል ” – የቡናዬ ቤተሰቦች
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ መቅሬዲ ቀበሌ ነዋሪዋና የቀድሞ የእግርኳስ እና ቦክስ ስፖርቶች በክልል ደረጃ ተወዳዳሪ አሁን ላይ ታታሪ ነጋዴ ቡናዬ ብርቅነህ በትናንትናው ዕለት ከኮሬ ዞን ወደ አጎራባች ምዕራብ ጉጂ ዞን ለገበያ በመጓዝ ላይ እያለች እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደሏን ቤተሰቦቿ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
የቡናዬ ወላጅ አባት አቶ ብርቅነህ ባሩድ እና ታላቅ ወንድሟ መምህር አዳነ ብርቅነህ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ለቲክቫህ በሰጡት ቃል፥ ቡናዬ ገና የ29 ዓመት ወጣት መሆኗን የቀድሞውን የደቡብ ክልልን በመወከል የቦክስና እግር ኳስ ተወዳዳሪ የነበረች ስፖርተኛ እንደነበረች ግለጸዋል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቀንድ ከብት እንዲሁም የሸቀጣሸቀጥ ነጋዴ በመሆን እየሰራች እንደነበር ጠቁመው በትናንትናው ዕለት ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋላና ሻሞሌ ሺዳ ቀበሌ ወደ ሚገኘው ፋታ ገበያ በመጓዝ ላይ እያለች በጥይት ተመታ መገደሏንና በሬና ፍየሎችን ለመግዛት የያዘችዉ ከ600 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም የእጅ ስልኳ መዘረፉን ተናግረዋል። ቡናዬ የ4 ዓመት ልጅ እናት እንደነበረች የገለፁት ቤተሰቦቿ ፥ ሴት ልጅ በዚህ ሁኔታ ስትገደል ይህ የመጀመሪያው መሆኑንና የሁለቱ ዞን መንግስታት የልጃቸዉን ገዳዮችን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
የኮሬ ዞን ፖሊስ ምን አለ ? ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸው የኮሬ ዞን ፖሊስ አዛዥ ም/ኮማንደር ሲዳሞ ማዳሞ ፤ በምዕራብ ጉጂና ኮሬ ዞኖች አዋሳኝ አከባቢ ወ/ሮ ቡናዬ ብርቅነህ በኮሬ ዞን ኬሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ታካሚ የነበረችን የምዕራብ ጉጂ ነዋሪ አንዲት እናት በሞተር ጭና ወደ ጋላና ወረዳ ሻሞሌ ሺዳ ፋታ ገበያ በመጓዝ ላይ እያለች (ከታማሚዋ ጋር ምንም ዝምድና የሌላት ሲሆን እየሸኘቻት ነበር) ለጊዜው ማንነታቸዉ ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት ተፈፅሞባቸዉ ሕይወቷ ማለፉን ተናግረዋል።
የገላና ወረዳ ፖሊስ አስክሬኑን ለኮሬ ዞን ማስረከቡን ገልፀው አብራት የነበረችው ግለሰብ ተርፋ ወደ ቤተሰቦቿ መወሰዷ እንደተነገራቸው ገልፀዋል። በአከባቢው የሚንቀሳቀስና እራሱን ‘ ሸኔ ‘ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ሃይል ቢኖርም የገዳዮችን ትክክለኛ ማንነት ለመለየት ግን የሁለቱ መዋቅር ፖሊስ በትብብር እያካሄደ ያለዉን ምርመራ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የገለላና ወረዳ ፖሊስ ምን አለ ? ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ ለማግኘት ወደ ገላና ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፐክተር ባራቃ ሀንቆ የእጅ ስልክ በተደጋጋሚ ቢደዉልም ስልኩ ባለመነሳቱ ለጊዜው ምላሻቸዉ አልተካተተም።