ላልተገራ ሥልጣን መታዘዝ እና ከአንባገነናዊ ባህሪ ጋር መዋሃድ፤ (ያሬድ ኃይለ ማርያም )
Obedience to authoritarian and internalization of authoritarian attitudes
+++++
“Blind obedience to authority is the greatest enemy of truth”
Albert Einstein
እንደምን ከረማችሁ የመልዕክተ ቅዳሜ ታዳሚዎች? አሰልሳ ብቅ ባለችው የዛሬዋ መልዕክተ ቅዳሜ ዋነኛ የትኩረት ነጥብ አንድ ማህበረሰብ ከአምባገነናዊ ሥርዓቶች ሳይላቀቅ ለረዥም ጊዜ በአፈና ውስጥ ሲቆይ እና በግፍ፣ ጭካኔ እና ሰቆቃ ውስጥ ሲኖር ከገዢዎቹ ከሚወርሳቸው ነገሮች አንዱ በሆነው ግፍን የመላመድና አንባገነናዊ ባህሪን የመላበስ ዝንባሌ ላይ የሚያተኩር ይሆናል፡፡
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ልጽፍ ያሰብኩት ያለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሃሳቡ የመነጨው የብልጽግና አገዛዝ በአለባበሳችሁ ባህልን እና ልማድን አጉድፋችኋል በሚል ለተወሰኑ ቀናት ወይም ከሳምንት በላይ ለቆየ ጊዜ ያሰራቸውን ቲክቶከሮች ተከትሎ በማህበረሰባችን በጉል የነበረው ግብረ ምላሽ ያጫረብኝ ነገር ነበር፡፡ ቲክቶከሮቹ የአገሪቱን ባህል፣ ወግ እና ልማድ በሚጥስ መልኩ ለብሰው በአደባባይ በመታየታቸው በወንጀል ጠርጥሬ አስሬያቸዋለሁ ብሎ የፌደራል ፖሊስ መግለጫ ሲሰጥ በደቦ እልል እያለ ድጋፉን የሰጠው አብላጫው የማህበረሰባችን ክፍል ልጆቹ ሲፈቱ እና መንግስት ለምን እና እንዴት ሊፈታቸው እንደቻለ ምንም መግለጫ ሳይሰጥ ሲቀር ደግሞ ያሁሉ የባህል ተቆርቋሪ እና ተሟጋች እንዴት ተፈቱ? የወንጀሉሱ ጉዳይ? ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን አለማንሳቱ አግራሞት ስለጫረብኝ ነው ርዕሱን ሰፋ ባለ መንገድ ከማህበረሰብ ባህሪ ጋር በማያያዝ ልመለስበት የወደድኩት፡፡
የልጆቹን ጉዳይ ላቆየውና ከላይ በርዕሱ ላይ እንደገለጽኩት አንድ ማህበረሰብ ወይም የአንድ አገር ሕዝብ ምን ሁኔታዎች ሲገጥሙት ነው እራሱን ከአገዛዝ ሥርዓት ጋር አዋህዶና አስማምቶ፣ አፈናን ተላምዶ እና ግፍን እንደ እለተ ተዕልተ ክስተት ቆጥሮ መኖር የሚችለው? አንድ ሕዝብ ምን ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው አንባገነናዊ ሥርዓትን እንደ ትክክለኛ ወይም ትክክለኛ ባይሆንም እንኳ እንደ አስፈላጊ መንግስታዊ ሥርዓት አድርጎ በመቆጠር ግፍን ከማንጠፍ ይልቅ መላመድን፣ አንባገነኖችን አሽቀንጥሩ ከላዩ ላይ ከማውረድና በነጻነት ከመኖር ይልቅ የእድሜ ልክ ባርነትን፣ ግዞትን እና አፈናን የተፈቀደለት የኑሮ ዘየው አድርጎ በመውሰድ ይህንኑ ባህሪውን ለልጅ ልጆች እያወረሰ ግፍን የሚያጸናው? የሚሉት ጥያቄዎች ላይ ላተኩር፡፡
ከዚህ በፍት “ግፍን መላመድ”፣ “እውነታን የመሸሽ በሽታ”፣ “አፈናን በዝምታ ማጽናት” እና መሰል ርዕሶች ላይ ባካፈልኳቸው አጫጭር የሁፎች እና ምልከታዎች ላይ ደጋግሜ ያነሳኋቸውን አንዳንድ ነገሮች እዚህ ብደግማቸው አስፈላጊ መስለው ስለታዩኝ ነውና ይቅር በሉኝ፡፡
በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለረዥም ዘመን በግፍ እና አፋኝ አገዛዝ ውስጥ ታምቆና ተጨቁኖ የሚኖር ማህበረሰብ እያደር እራሱን ከግፍ እና አፈና ጋር ያላምዳል፡፡ በተለይም ከትውልድ ትውልድ ተሸጋጋሪ በሆነ የአገዛዝ ሰንሰለት ውስጥ የቆየ ሕዝብ፤ ማለትም አያት፣ አባትና እናት ከዛም ልጆቻቸው ተወራራሽ በሆኑ የአገዛዝ ሥርአት ውስጥ ለመኖር የሚገደዱበት ሁኔታ ከተፈጠረ በዛ ማህበረሰብ ውስጥ ነጻነት፣ ፍትህ፣ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ርትዕ እና እውነት የሚባሉ ነገሮች አሻራቸው እየደበዘዘ፣ ትርጉም እያጡና ዋጋቸውም እየኮሰሰ የማይደረስባቸው ነገሮች ወይም እንደ ጉም እየተበተኑ የሚመጡ ሃሳባዊ ነገሮች ብቻ ይሆናሉ፡፡
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ማህበረሰብ ግፍን፣ አፈናን፣ የፖለቲካና እና የባህል ጭቆናዎችን፣ የኢኮኖሚ ኢፍትሃዊነትን እና የማህበራዊ ፍትህ መታጣትን የተለመዱ፣ የተዋሃዳቸው፣ ለእርሱ የሚገቡት፣ አንዳንዴት ተገቢ እንደሆኑ አድርጎ ወደማሰብ እና ለአንባገነናዊ ሥርአት ጸጥ ለጥ ብሎ መገዛትን (strict obedience to authority) እንደ ትክክለኛ እና የጨዋ ሕዝብ መገለጫ አድርጎ ይወስደዋል፡፡ እየቆየም ራሱን ያለ አምባገነን ሥርአት እና ያለ አፈና መኖር የማይችል ሕዝብና አገር አድርጎ ይቆጥራል፡፡ የአገዛዝ ሥርአቶቹ እንዴት መተንፈስ እንዳለበት፣ እንዴት ማውራት እንዳለበት፣ እንዴት መልበስ እንዳለበት፣ እንዴት ባህሉን ማክበር እንዳለበት፣ እንዴት ማሰብ ጭምር እንዳለበት በትዕዛዝ መልክ የሚሰጡትን የፖለቲካ አስተምህሮት (political indoctrination) ምንም መመርመርና መጠየቅ ሳያስፈልገው እንደወረደ ወደሚቀበልበት ደረጃ ላይ ያወርዱታል፡፡ የአገዛዝ ሥርአቱን ከመንግስትነት አልፈውም በሕዝብ ላይ የጥብቅ እና ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የወላጅነት (strict parenting) ባህሪም እንዲላበስ ይፈቅዱለታል፡፡
የረዥም ጊዜ ታርካችንን እናቆየውና የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ንጉሳዊ አስተዳደርን፣ የደርግ ኢሰፓን፣ የወያኔ ልማታዊ መንግስትን እና የብልጽግና የመደመር እሳቤን አከታትሎ ያስተናገደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደረጃው ይለያይ እንጂ ላለፉት 80 እና 90 አመታት በአፈና ውስጥ ነው የኖረው፡፡ ንጉሱም፣ ደርግም፣ ወያኔም፣ ዛሬ ደሞ ብልጽግናም የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፍትህ፣ ከዲሞክራሲ እና ከእኩልነት ሚዛን አርቀው ርሃብን፣ ጦርነትን፣ ድህነትን እና ጠመንጃን ዋነኛ የመግዣ ሥልት አድርገው በመጠቀም የእድሜ ልክ ግዞተኛ አድርገውት ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለ አገር ቢሆንም የአገሩ ባለቤት፣ በአገሩ ላይ ፈላጭ ቆራጭ እና የሥልጣን ባለቤት ሆኖ አያውቅም፡፡ በብዙ ሺዎች ምሁራንን ያፈራ አገር ቢሆንም ባስተማራቸው ምሁራን፣ በእውቀትና በጥበብ የመመራት እድል ገጥሞት አያውቅም፡፡ ጉዞው የቁልቁለት በመሆኑ በንጉሱ ዘመን የነበረው ለዘብተኛ አፈና በደርግ ጊዜ ጥርሱን አሹሎና አግጦ በመምጣቱ ብዙ የአገሪቱን ምርጥ ጭንቅላቶች በጥይት እያፈረሰ አገር አደንቁሮ የመግዛት መንገዱን ገና ከጅምሩ በነብር የተያያዘው፡፡ ይሄው ምሁር ጠል የአገዛዝ ሰንሰለት በወያኔም ጊዜ ቀጠለ፡፡ ባልነጠፈው ግፍ ላይ ወያኔ የዘር ተኮር ፖለቲካዊ መርዝ ጨመረበት፡፡ መርዙ ከፖለቲካችንም አልፎ በሁለመናችን ከተዋሃደ በኋላ በብልጽግና ክሽፈት ወደ እርስ በርስ መጨራረሱ አመራ፡፡
እንግዲህ የንጉሱን 43 አመታት፣ የደርኝ 17 አመት፣ የወያኔን 27 አመት እና የብልጽግናን 7 አመታት ስንደምራቸው ወደ 94 አመታት ይቆጠራሉ፡፡ ሦስት አራት መንግስት አይቻለሁ የሚሉት ዛሬ በዘጠናዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ አዛውንቶች ሙሉ ዘመናቸውን በአፈና አገዛዝ ውስጥ ነው የኖሩት፡፡ የእነሱ ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸውም እንዲሁ ሁለት ወይም አንድ አንባገነን እድሜያቸውን የቀረጠፉባቸው ናቸው፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ቢበዛ በአምሳ አመታት ውስጥ ከምዕራባዊያን ቅኝ ገዢዎች ተላቀው ዛሬ በብዙ መልኩ ከእኛ የተሻለ የነጻነት አውድና በራስ የመተማመን መንፈስ ውስጥ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እኛን ደግሞ የተመለከትን እንደሆነ ከዚህ በፊት እንደጻፍኩበት የአድዋን የነጻነት በአል በድምቀት የምናከበር ነገር ግን ከቅኝ ገዢ ካድሬዎች ነጻ መውጣት ያቃተን ምርኮኞች ሆነን ከ90 አመታት በላይ በአንባገነኖች የግዞት ሰንሰለት ተተብትበን እንገኛለን፡፡
የአንባገነናዊ የአገዛዝ ሰንሰለት ሕዝብን የግፍ ምርኮኛ አድርጎ ለማቆየት ከዚህ የሚከተሉትን ሥልቶች በዋነኝነት ይጠቀማል፤
1ኛ/ ከልጅነት እስከ እውቀት እና ምናልባትም እስከ ሞት ድረስ በአፋኝ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መቆየት (Childhood Socialization) የመጀመሪያው ነው፡፡ ከላይ እንዳልኩት በአፋኝ ሥርአት ውስጥ ተወልዶ፣ አድጎ፣ ጎልምሶ፣ ሸምግሎ፣ ልጆችና የልጅ ልጆች አፍርቶ መሞት፡፡ መልጅነት እድሜ ጀምሮ እጅግ አስከፊ (harsh)፣ ቅጣት ላይ ባተኮረ ስነልቦና (punitive) እና በልጆችና በወላጆች መካከል ያለውም ግንኙነት የፈላጭ ቆራጭ (domineering parenting) እንዲሆን በማድረ ልጆች ጠያቂ እንዳይሆኑና የታዘኡትን ነገር ብቻ እንዲፈጽሙ በማስተማር (learn to obey without question) አፈናን እንዲለማመዱ ማድረግ አንዱ ስልት ነው፡፡ በእንዲህ ያለው ሁኔታ ያደጉ ልጆች ሁሌም ታዛዥና ጠያቂዎች ባለመሆናቸው ለአገዛዝ ሥርዓት የታጩ ታዛዦችና ምቹ ናቸው፡፡
2ኛ/ ጥልቅ ፍርሃት መፍጠር እና ባልተጨበጡ ስጋቶች ውስጥ መውደቅ (Fear and threat Perception)፤ ይህ ብዙ የአንባገነን ሥርአቶች ልክ እንደ የሕዝብን ስሜት፣ ቁጣ እና ጥያቄ አፍነውና ተቆጣጥረው የሚያቆዩበት ዋነኛ ሥልት (coping mechanism) ነው፡፡ ሕዝብን ሁሌ ስጋት ውስጥ በመጣል የውጪ ጠላት እንዳለው እንዲያስብ (እገሌ አገር ሊወረን ነው)፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በመፍጠር እና በፍጥነት የሚለዋወጡ ማህበራዊ ቀውስ አስከታይ ልወጦችን በመፍጠር ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋና ሽብር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፡፡
3ኛ/ ሁሉም የአገዛዝ ሥርአቶች ከሌላው እንለያለን ብለው ሕዝቡን አስገድደው የሚግቱት የፖለቲካ ትርክት፣ እሳቤና ስብከት (Political Indoctrination) ስላላቸው ሁሉም ዜጋ በተሰመረለት የእሳቤ መስመር ላይ ብቻ እንዲቆም ማድረግ (official line of the government)፡፡ መንግስት ካሰመረው መስመር መውጣት ወይም ማፈንገጥ እንደ አገር ክህደት እንዲቆተር ማድረግ፡፡ አብይ ያልተደመረ ሁሉ የአገር ጠላት ነው ብሎ ያሰመረው የቅርቡን መስመራችንን መጥቀስ ይቻላል፡፡
4ኛ/ ወጥ የሆነ እና አንድ ገዢ ሃሳብ ብቻ እንዲንሰራፋና በማህበረሰቡ ውስጥም እንዲሰርጽ በማድረግ ሌሎች ተፎካካሪ ሃሳቦች ጭርሱኑ እንዳይኖሩ ማድረግ ወይም ማክሰም (Cognitive Rigidity) ሌላው ስልት ነው፡፡ የዚህ ስልት ዋነኛው አላማ እጅግ አንባገነን የሆኑ ግለሰቦች (High-authoritarian individuals) ሃሳብ ብቻ ገዢና ብቸኛ ሆኖ እንዲወጣ በማድረግ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ቡድን የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ የአብይ ተከታታይ የመደመር ፍልስፍና በሚል የተሰነዱ መጽሃፎች ዋነኛ ግባቸውም ይሄው ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው በአንድ ሕዝብና አገር ላይ የሚፈራረኩ የአንባገነናዊ ሥርአቶች ማህበረሰቡን በቆይታ ውስጥ እራሱን ከግፍ አገዛዞች ጋር አላምቾና አዋህዱ እንዲያኖር የማድረጊያ ስልቶች ናቸው፡፡ ውጤታቸውም ግልጽና አስተማማኝም እንደሆነ ብዙ ርቀት ሳንሄድ ይህ ሁሉ መከራና ሰቆቃ የሚወርድበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግፈኞቹ የሚሰተውን እድልና አንዳንዴም ግፈኞቹን ሺ አመት ይግዙኝ እያለ ደጅ የሚጠናበት ስነ ልቦናው ከየት እንደመነጨ ያሳያል፡፡ እራሱን ከግፍ ጋር ያዋሃደ ማህበረሰብ ከዚህ የሚከተሉት መገለጫዎችን ያሳያል፤
ሀ/ ለሚመጣው አንባገነናዊ ሥርአት ሁሉ እራሱን አዋርዶና አኮስሶ እንዲረግጡት እራሱን መሬት ላይ የማነጠፍ ባህሪ ይላበሳል (Authoritarian Submission)፡፡ መንግስትን ተደብቆ ቢያማ እንኳ በአደባባይ አይተችም፣ ለባለሥልጣናት በሚያሳየው እጅግ ተለማማጭነትና መንበርከክ የተነሳ ለሚፈጽሙበት ግፍ ሁሉ የመቀበል እውቅናን ይሰጣል፡፡
ለ/ የተለመዱ ወጎችን፣ ባህሎችን፣ ሃይማኖቾችን እና ልማዶችን በመጣስ እራሳቸውን ከማህበረሰቡ ጫና ነጻ በማውጣት ሃሳባቸው በነታነት የሚገልጹ፣ በአለባበሳቸውም ሆነ በሃሳብ መስመራቸው ወጣ ያሉ ግለሰቦችን እያደነ የጥቃት ኢላማ ያደርጋል፣ ያወግዛል፣ ያዋርዳል አንዳንዴም የደቦ እርምጃ በመውሰድ እና አንዳንድ ገደቦችንም በመጣል ከአንባገነን ገዢዎቹ በከፋ ሁኔታ የአገዛዝ ባህሪ ይላበሳል፡፡ (እዚህ ላይ የቲክቶከሮቹን ጉዳይ ማየት ይቻላል፡፡)
ሐ/ ጽንፍ የያዘ የሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ተቆርቋሪ በመሆኑ (Conventionalism) ለውጦችን መቃወም፣ መንቀፍ እና ዘመኑን ለሚዋዡ አስተሳሰቦች ጭምር በተቃርኖ መቆም የሚታይበት ማህበረሰብ ይሆናል፡፡
እንዲህ አይነት ባህሪዎችን ከአገዛዝ ሠንሰለት የወረሰ ማህበረሰብ ለሁሉም አይነት ለውጦች ሁሌም ተገዳዳሪ ነው የሚሆነው፡፡ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ዜጎች ነጻነት እና ሰብአዊ መብቶች ጭምር ከመጣስና የአገዛዝ ሥርአቶቹም የዜጎችን መብት ሲጥሱ አብሮ ድጋፍ በመስጠት አፈናን እና ግፍን በራሱ ላይ ያጽናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የደቦ ፍርድ እንዲስፋፋ ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች አንዱ ይህ የማህበረሰቡ የአገዛዝ ባህሪን፣ የአፋኝነት ስነ ልቦናን እና ጭካኔን በሂደት ከአገዛዝ ሥርአቶቹ እየወረሰ ከመምጣቱ ጋር እንደሚያያዝ የሚያሳዩ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ yared hailemariam