ለአሜሪካ ፍሎሪዳው አገር አቋራጭ ውድድር ከሚሳተፉ አትሌቶች፣አሠልጣኞች እና አመራሮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ቪዛ ተከለከሉ
አሁን ማምሻውን እጅግ አስደንጋጭ ዜና ደርሶናል፤እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 10 በአሜሪካ ፍሎሪዳ ታላሃስ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው 46ኛው ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ካሉ አትሌቶች፣አሠልጣኞች እና አመራሮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ቪዛ መከለከላቸው ታውቋል።
ታማኝ የፌዴሬሽን ምንጮቻችን እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ በ46ኛው የአሜሪካ ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙት አትሌቶች፣አሠልጣኞች እና አመራሮች ቪዛ ለማግኘት ቀደም ብለው ፎርማሊቲውን አሟልተው ዛሬ ሽሮሜዳ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቢጓዙም ካመለከቱት አመልካቾች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቪዛ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አጥቶ መከለከላቸው ነው ታማኝ ምንጮቻችን ያደረሱን መረጃ የሚጠቁመው።
የአሜሪካ መግቢያ የቪዛ ማመልከቻቸው ውድቅ ከሆነባቸው አትሌቶችና አሠልጣኞች በተጨማሪ በቅርቡ ወደ ፌዴሬሽኑ የፅ/ቤት ኃላፊነት የመጡት አመንሲሳ ከበደ(ዶ/ር) የሚገኙበት ሲሆን ከእሳቸው በተጨማሪ ፊዚዮቴራፒስቶችም የቪዛ ማመልከቻ ጥያቄያቸው ውድቅ ከሆነባቸው ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።
የቪዛ ጥያቄያቸው ውድቅ የሆነባቸውና የተፈቀደላቸው እነማን እንደሆኑ የጠየቅናቸው ምንጮቻችን ስሜታቸው እንዳይጎዳ ስማቸውን መግለፅ ባለመፈለጋቸውና ይቆይ በማለታቸው በዚህ ዘገባ ውስጥ ማንነታቸውን አላካተትንም።
የአሜሪካ ኤምባሲ አመልካቾቹ ወደ አሜሪካ የሚጓዙት ለውድድር እንደሆነና አንዳንዶቹም የጉዞ ታሪክና በአትሌቲክስ ትልቅ ስምና ንብረት(አሴት) ያላቸው እንደሆነ እየታወቀ ለምን ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን አትሌቶች፣አሠልጣኞች እና የአመራሮቹን የቪዛ ጥያቄ ለምን ውድቅ እንዳደረገ የተገለፀ ነገር ባይኖርም ቪዛ የሚያሠጥ አሳማኝ ምክንያት አላገኘሁም በማለት ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን”አልተሳካም”በሚል አጭር መልስ እንደመለሳቸው ነው የተሠማው።
እነዚሁ ታማኝ ምንጮቻችን ጨምረው እንደገለፁልን የጉዞው አላማ እየታወቀ ኤምባሲው ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ቪዛ መከልከሉ የፌዴሬሽኑን አመራሮች ክፉኛ ያስደነገጠ ሲሆን አትሌቶቹንና አሠልጣኞቹንም ስሜት እንደጎዳ ነው የተሠማው።
ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ችግሩን ፈትቶ ቪዛ ለማግኘት የተለያየዩ ስራዎች እየተሠሩ ሲሆን በሚኒስቴር መ/ቤቱና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የዘገባውን ተዓማኒነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ይመለከታቸዋል ያልናቸው የፌዴሬሽኑ አመራሮች የእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም አንዳቸውንም ለማግኘት አልቻልንም፤በቀጣይ የሚመለከታቸውን አነጋግረን ተጨማሪ መረጃ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።