የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ የአሜሪካን ግሪን ካርድ ሎተሪን (ዲቪ) አገደ። የዲቪ ሎተሪ ፕሮግራም የታገደው፣ ከቀናት በፊት አንድ በዲቪ ሎተሪ ወደ አሜሪካ የገባ የፖርቹጋል ተወላጅ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በኹለት ሰዎች ላይ ከፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ እንደኾነ ተገልጧል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ በዲቪ ፕሮግራም ወደ አገሪቱ በሚገቡ ሰዎች ምክንያት በአሜሪካዊያን ላይ ከእንግዲህ ጉዳት እንዳይደርስ ለማረጋገጥ እገዳውን መጣል እንዳስፈለገ ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ ለተለያዩ አገራት ዜጎች በየዓመቱ 50 ሺሕ የመኖሪያና ዜግነት ማግኛ ቪዛዎችን ሲሠጥ የቆየ ሲኾን፣ ባለፉት 30 ዓመታት ከ3 ሺሕ 600 በላይ ኢትዮጵያዊያን የእድሉ ተጠቃሚ ኾነዋል።