የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለአልጀርሱ ስምምነት መከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ እንዲያሳዩ ጥሪ አደረጉ። ጉተሬዝ ይህን ጥሪ ያደረጉት፣ የአልጀርሱ ስምምነት የተፈረመበትን 25ኛ ዓመት አስመልክተው በቃል አቀባያቸው ስቲፋኒ ዱጃሪክ በኩል ትናንት ባወጡት መግለጫ ነው። ጉተሬዝ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ባሁኑ ወቅት የተፈጠረው አዲስ ውጥረት ቀጠናዊ ሰላምን ሊያውክ ይችላል በማለት አስጠንቅቀዋል። የአልጀርሱ ስምምነት የሁለቱን አገራት ድንበር ለማካለል ማዕቀፍ ያስቀመጠና ለአገራቱ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር መሠረታዊ መርሆዎችን በድጋሚ ያረጋገጠ መሆኑንም ጉተሬዝ ጠቅሠዋል። ተመድ ለአልጀርሱ ስምምነት ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው የገለጡት ጉተሬዝ፣ የሁለቱ አገራት መሪዎችም ከሰባት ዓመታት በፊት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በስምምነት ማረጋገጣቸውን አስታውሰዋል። ጉተሬዝ አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከቀጠናዊ እና ዓለማቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት ትብብር እንዲያካሂዱ ጠይቀዋል።