አብዱራህማን መሃዲ የሚመሩት የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) አንጃ፣ አዲሱ የአሜሪካ ብሄራዊ የደኅንነት ስትራቴጂ በቀጠናው ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ቡድኖችን ያገለለ በመሆኑ ግጭቶችን ፈጽሞ አይፈታም በማለት ተቸ። ቡድኑ፣ አሜሪካና አጋሮች በቀጠናው ሰላም ማስፈን ከፈለጉ፣ የሰላም ስምምነቶች በተመረጠ ሁኔታ ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ፣ የሶማሌ ሕዝብን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደጨፈለቀው እና ኢትዮጵያ ለኤርትራ፣ ለሱዳን፣ ለሶማሊያ እና ለግብጽ የምታሳየው የጠቅላይነት አካሄድ ለቀጠናዊ ሰላም ጠንቅ መሆኑን ማወቅ አለባቸው ብሏል። ቡድኑ አያይዞም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ የአለመረጋጋት ምንጭ ሆኗል ብሏል። ኦብነግ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ፌደራል መንግሥቱ የሚያካሂደውን አፈና እና ጦርነት ችላ ብሏል በማለት የወቀሠው ቡድኑ፣ መንግሥት በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ሌሎች ክልሎች የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ሁሉ ሆነ ብሎ ተቃውሞንና ብዝሃነትን ለማጥፋትና የብሄሮችን መብቶች ለመጨፍለቅ ያለመ ነው በማለት ከሷል።