በሆሮ ጉዱሩ በታጣቂዎች የተገደሉት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት አስከሬን አለመገኘቱ ተነገረ

 

 በታጣቂዎች ከተገደሉት መካከል መልአከ ኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ዱፋ

የፎቶው ባለመብት,EOTC

የምስሉ መግለጫ,በታጣቂዎች ከተገደሉት መካከል መልአከ ኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ዱፋ

በኦሮሚያ ክልል፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሁለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በታጣቂዎች ከተገደሉ ቀናት ቢቆጠርም አስከሬናቸው እንዳልተገኘ ተገለጸ።

ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ. ም. ቀሳውስቱ በሀራቶ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓል ታድመው ወደ ሻምቡ ከተማ እየተመለሱ ሳለ ነበር መኪናቸው በታጣቂዎች እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ወደ ጫካ ተወስደው የተገደሉት።

በጉዞው ላይ አብረዋቸው ከነበሩት ቀሳውስት አንደኛው “በጅማ ገነቲ አካባቢ የቅድስት ማርያም ክብረ በዓል ነበር። ከሥነ ሥርዓቱ ስንመለስ 9 ሰዓት አካባቢ ታጣቂዎች አስቆሙን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እኝህ የዐይን እማኝ በመኪናው ተሳፍረው የነበሩት “20 ሰዎች” እንደሆኑ ገልጸው፤ “ከ20ዎቹ መካከል አስሩን አስወርደው ወደ ጫካ ወሰዷቸው። የተቀሩት በበቆሎ ማሳ ውስጥ ተበታትነው በመሮጥ አመለጡ” ብለዋል።

ቄሱ እንደገለጹት፤ ታጣቂዎቹ በሻምቡ ከተማ መግቢያ ላይ መንገድ ዘግተው እና ስናይፐር መሣሪያ ይዘው ነበር።

ወደ ጫካ አካባቢ ከተወሰዱት ቀሳውስት መካከል የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ ሕጻናት እና መዘምራን እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።

“ጫካው ውስጥ ወስደው በስም ጠሯቸው። አንድ በአንድ በስም ከጠሯቸው በኋላ ልጆቹ ታጣቂዎቹ ከያዙት የስም ዝርዝር ውስጥ ስላልነበሩ ለቀቋቸው” ብለዋል።

“አራቱ ሰዎች የሆሮ ጉዱሩ አገረ ስብከት ዋና ኃላፊ መልአከ ኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ዱፋ፣ ቄስ ቀናሳ ጊዲሳ፣ ቄስ ደሳለኝ ነሞምሳ እና ቄስ ባቡሽን ጠሩ ናቸው” ሲሉም በስም ጠቅሰዋል።

ታጣቂዎቹ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው እና በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከእገታዎች እና ከግድያዎች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ተጠያቂ ቢደረግም ክሶቹን ያስተባብላል።

አሁን ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ በቀረበበት ክስ ላይም ምላሽ አልሰጠም።

ከቀሳውስቱ መካከል ሁለቱ ታግተው መለቀቃቸውን የዐይን እማኙ ገልጸዋል። ቄስ ዱጉማ ዱፋ እና ቄስ ደሳለኝ ነሞምሳ ደግሞ መገደላቸው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክት አክለዋል።

ታጣቂዎቹ “ሁለቱን ቀሳውስት ከገደሉ በኋላ ሁለቱን አርብ ዕለት ለቅቀዋቸዋል” ብለዋል።

ለቀሳውስቱ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት በቤተ ክርስቲያኗ የተደረገ ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንዳይፈጸም ግን አስከሬናቸው እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

ሌላ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የሚያገልግሉ እና ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ቀሲስ ግድያው “የታቀደ” እንደነበረ ተናግረዋል።

“ከታገቱ በኋላ እንዲለቀቁ ለመጠየቅ ቤተሰቦቻቸው ስልክ ደውለዋል። እንደማይለቋቸው እና አስከሬናቸውንም እንደማይሰጡ ታጣቂዎቹ ገልጸዋል” ብለዋል።

በአካባቢው ባለው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል እንደነበር እና የተለያዩ ቡድኖች ደጋፊዎች እና ነቃፊዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

ግድያው ከክፍፍሉ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ቢያስቀምጡም ቢቢሲ ጉዳዩን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

“እነዚህ ሰዎች ፖለቲከኞች አይደሉም። ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት የላቸውም።ሰላም ለማምጣት ነው የሚጥሩት። ታጣቂዎቹ ማን እንደሆኑ እንኳን ስላላወቁ ስማቸውን እየጠሩ ነበር ማንነታቸውን የለዩት ” ሲሉ ተናግረዋል።

ቀሳውስቱ ስማቸው ተመዝግቦ ሲጠራ እንደነበር በመጥቀስ ጥቃቱ “የተቀነባበረ እና ቀሳውስቱን ዒላማ ያደረገ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ቀሳውስቱ “በኦሮምኛ እንጂ በአማርኛ መስበክ የለባቸውም” ማለታቸውን የቢቢሲ ምንጭ ጠቁመዋል። ሆኖም ግን የተገደሉት ሁለቱም ቀሳውስት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው።

የሆሮ ጉዱሩ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ዱጉማ ዱፋ ማኅበረሰባቸውን በቀናነት ሲያገለግሉ እንደነበር የዐይን እማኞቹ አክለዋል።

ከግድያው ጋር በተያያዘ በከተማው ውስጥ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ቀሳውስት መንግሥት ስለ ግድያው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የሻምቡ ከተማ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ የሟቾቹን ስም ጠቅሶ በታጣቂዎች ተወስደው መገደላቸውን አስታውቋል።

የምሥራቅ ሐረርጌ፣ የምሥራቅ ወለጋ እና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የአገረ ስብከት መሪ ሐዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ስለ ግድያው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።