ባለፈው ዓመት የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ማቆም አድማ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ያስተባበረው ቡድን፣ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ሁለተኛ ዙር የሥራ ማቆም አድማ ጠራ። ቡድኑ፣ ጤና ሚንስቴርም ሆነ የክልሎች ጤና ቢሮዎች የጤና ባለሙያዎችን ሕጋዊ እና የኅልውና ጥያቄዎች እስካልመለሱ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በተለያዩ የማስተማሪያና ሌሎች ሆስፒታሎች የሚሠሩ ጥቂት ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ መስተካከሉን ተከትሎ የስራ ማቆም አድማውን ለመቀላቀል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ተረድቻለሁ ያለው አስተባባሪ ቡድኑ፣ ሁለተኛውን የስራ ማቆም አድማ የማይቀላቀሉ ባለሙያዎች ወደፊት ለሚደርሱባቸው የመብት ጥሠቶች ሃላፊነት አልወስድም በማለት አስጠንቅቋል።
ቡድኑ፣ በተለያዩ ክልሎች የጤና ባለሙያዎች ማስፈራራት እና የእገዳ ዛቻ እየደረሰባቸው ይገኛል በማለትም ድርጊቶቹን አውግዟል።