ኢትዮጵያ በጋዛ የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ እንድትሳተፍ ከአሜሪካ ጥሪ ቀረበላት

ኢትዮጵያ በጋዛ የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ እንድትሳተፍ ከአሜሪካ ጥሪ እንደቀረበላት ተገለጸ።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከቀናት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸው መገለጹ ይታወሳል።

በወቅቱ በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት ለቀጠናዊ መረጋጋት እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለመገንባት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የገለጹበት እንደነበር ስቴት ዲፖርትምንት በወቅቱ ገልጾ ነበር።

ዛሬ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ይዞ በወጣው ዘገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ውይይት ወቅት ኢትዮጵያ በጋዛ ሰርጥ በሚቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይል ተሳታፊ እንድትሆን መጠየቃቸውን አንስቷል። ይሁን እንጂ ዘገባው የኢትዮጵያን ምላሽም ሆነ ዝርዝር ጉዳዮችን አላካተተም።

ማርኮ ሩቢዮ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫቸው “ያነጋገርናቸው ሀገራት ሁሉም በሚባል ደረጃ ወታደሮቻቸውን ለመላክ ምን ዓይነት ግዳጅ ውስጥ እንደሚገቡ እና የፋይናንስ አቅርቦቱ ምን እንደሚመስል ማወቅ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

ማርክ ሮቢዮ ይህንን የተናገሩት ፓኪስታን ወታደሮቿን ለማሰማራት ፈቃደኝነቷን መግለጿን ተከትሎ በቀረበላቸው ጥያቄ ውቅት ሲሆን የፓኪስታንን ጥያቄ “እያጤነው ነው” ሲሉም መልሰዋል።

አብዛኞቹ የአረብ ሀገራት ወታደሮቻቸውን ለመላክ “የፍልስጤም መንግስት ምስረታ የጊዜ ሰሌዳ በግልጽ እንዲቀመጥ” የሚል ጥብቅ ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጡ አንዳንዶቹ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ የእስራኤልን ወታደራዊ ፍላጎት ብቻ የሚያስፈጽም እንዳይሆን እና በሕዝባቸው ዘንድ “ተቃውሞ” እንዳያስነሳ ስጋት ገብቷቸዋል።

ማርኮ ሩቢዮ ሀገራት ወታደሮቻቸው ምን ዓይነት ግዳጅ ውስጥ እንደሚገቡ ሳያውቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አንጠብቅም ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የጋዛ ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይል (ISF) በዋናነት ሰብዓዊ እርዳታዎች ለተጎጂዎች እንዲደርሱ ጥበቃ ማድረግን፣ የሲቪል አስተዳደሩን መደገፍ እና አካባቢው ዳግም ለሽብር ጥቃት እንዳይውል ቁጥጥር ማድረግን ዓላማ ያደረገ ተብሏል።