አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ሰጥታ የነበረውን የጊዜያዊ ከለላ መብት አንስታለች።
የአሜሪካ የሃገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ክርስቲ ኖዬም ለኢትዮጵያ ተሰጥቶ የነበረው የጊዜያዊ ከለላ መብት መነሳቱን አስታውቀዋል።
አሜሪካ በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ወደ ሃገራቸው መመለስ ለማይችሉ ዜጎች ጊዜያዊ ከለላ (Temporary protected status) ትሰጥ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያም ይኸው መብት ነበራት።
አሜሪካ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በሃገሯ የሚኖሩ የሌሎች ሃገራት ዜጎች ጦርነትን ጨምሮ በአንዳንድ ምክንያቶች ወደመጡበት ሃገር መመለስ ለማይችሉ ሰዎች ይህንን ከለላ መስጠት ጀምራ ነበር።
ይህ ከለላ የሚሰጣቸው ዜጎችም የሃገራቸው ሁኔታ እስኪሻሻል በአሜሪካ የመኖርና የመስራት መብት ሲሰጣቸው ከአሜሪካ ከመባረር ይጠበቁ ነበር።
አሜሪካ” በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ግለሰቦች ደህንነት ላይ ስጋት አይፈጥርም” ያለች ሲሆን በዚህም የተነሳ ይኸው ከለላ መነሳቱን አስታውቃለች።
አሜሪካ ሌሎች በአሜሪካ ለመቆየት ህጋዊ መሰረት ካላቸው ኢትዮጵያውያን ውጪ የኢትዮጵያ ዜጎች በ60 ቀናት ከሃገሯ እንዲወጡ አሳስባለች።
ቀድመው ከአሜሪካ ለሚወጡ የትኬት ወጪያቸው እንደሚሸፈን፣ የ1000 ዶላር ጉርሻ እንደሚሰጥና ለወደፊቱ ህጋዊ የኢሚግሬሽን እድል እንደሚኖራቸው ገልፃለች።
ከፈረንጆቹ የካቲት 13 በኋላ ከለላው እንደሚያበቃ ገልፃ ያለ ከለላው በአሜሪካ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደምታስር እና ከሃገሯ እንደምታባርር አስጠንቅቃለች።
አሜሪካ ከሳምንታት በፊት ተመሳሳይ ከለላ የነበራቸውን የደቡብ ሱዳን ዜጎችን መብት አስንታለች።