የደቡብ ሱዳን በግዛቷ ውስጥ ግብጽ ጦር ሰፈር እንድታቋቁም ፈቃድ ሰጥታለች እየተባለ የሚነገር መረጃ ሐሰት መሆኑን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አስታወቀ።

BBC Amharic : የደቡብ ሱዳን በግዛቷ ውስጥ ግብጽ ጦር ሰፈር እንድታቋቁም ፈቃድ ሰጥታለች እየተባለ የሚነገር ሐሰት መሆኑን ዛሬ ጠዋት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አስታወቀ።

ከትናንት ጀምሮ የተለያዩ ምንጮች ግብጽ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ጦር ሰፈር እንዲኖራት ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት እንዳገኘች ሲናፈስ ነበር።

መረጃው የደቡብ ሱዳን መንግሥት በጥያቄው ተስማምቶ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስነው ፓጋክ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ጦር ሰፈሯን እንድታቋቁም ፈቅዷል የሚል ነበር።

“የተባለው ነገር ሐሰተኛ ዜና ነው። በሁለቱ አገራት ውስጥ ስምምነት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የደቡብ ሱዳን ጦር ሠራዊት ቀድሞ ያውቅ ነበር። ምንም አይነት ስምምነት አልተደረገም” ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከፍተኛ የጦር ባለስልጣን መናገራቸው ተዘግቧል።

የጦር ባለስልጣኑ ጨምረው እንደተናገሩት “ከኢትዮጵያ ጋር የመከላከያ ስምምነት ስላለን ያንን በመጣስ ምንም አናደርግም። ኢትዮጵያ የዛሬዋ ደቡብ ሱዳን እንድትመሰረት አስተዋጽኦ አድርጋለች” ሲሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት ገልጸዋል።

ቢቢሲ አዲስ አበባ ከሚገኘው የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ስለጉዳዩ መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ቢሆንም እስካሁን አልተሳካለትም።

ይህ ደቡብ ሱዳን፣ ግብጽ ፓጋክ በተባለው ግዛቷ ውስጥ የጦር ሰፈር እንድታቋቁም ፈቅዳለች የሚለው ዜና ጁባ ቲቪ እና ሳውዝ ሱዳን ኒውስ ናው በተባሉ መገናና ብዙኀን ላይ ከተሰራጨ በኋላ ነው ከፍተኛ ትኩረትን ያገኘው።

የጦር ሰፈሩ ይቋቋምበታል ተብሎ የተጠቀሰው ስፍራ ፓጋክ ደቡብ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢ ያለ ቦታ ሲሆን፤ ቦታው የአገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻር የሚመሩት ተቃዋሚው የሱዳን ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ጠንካራ ይዞታ ነው።

ወሬውን ትኩረት እንዲስብ ያደረገው ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብን በተመለከተ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር እያደረገችው የነበረው ድርድር መቋጫ ሳያገኝ በእንጥልጥል ባለበት ጊዜ መሆኑና ኢትዮጵያ ግድቡን በቀጣይ ወር በውሃ መሙላት ለመጀመር በምትዘጋጅበት ጊዜ መሆኑ ነው።