ከጠንካራ ሠላማዊ ትግል መቼም አታስቆሙንም!!! *ከ ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ ሕዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ‹አዲስ አበባ ትናገራለች› በሚል መሪ ሃሳብ የጠራው ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ይፋ ከተደረገበት ቀን አንስቶ በፓርቲው እና አመራሩ ላይ የስም ማጥፋት እና የማስፈራሪያ ፕሮፖጋንዳዎች በገዢው ፓርቲ ልሳናት በኩል ሲተላለፉ መቆየታቸውን ተመልክተናል፡፡
ፓርቲያችን የጠራው ስብሰባ አዳራሽ ለማከራየት ተስማምተው በነበሩ ሆቴሎች እና ሲኒማ ቤቶች ላይ በደረሰ ከፍተኛ ጫና ምክንያት እንዲሰረዝ ከተደረገ በኋላም የገዢው ፓርቲ ልሳናት እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ‹አጥፏቸው› የሚል ይዘት ያላቸውና ከተወሰነ ማዕከል በመመሪያ የሚወርዱ መሆናቸው የሚታወቅ የበቀቀን ጨኸት የሚመስሉ ፕሮፖጋንዳዎች መነዛታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የልጥፎቻቸው እና የውንጀላዎቻቸው ይዘትም ነገ በፓርቲያችን ላይ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ አመላካች
ነው፡፡
መሰል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ከሆዳቸው አንድ ስንዝር አርቀው ማሰብ የማይችሉ፣ የራሳቸው አቋም የሌላቸው፣ በተሰፈረላቸው ልክ የሚጮሁ የየስርኣቱ ተለጣፊዎች እና በሞቀበት አዳሪዎች ነገ ትክክለኛ የፍትሕ ስርኣት ሲሰፍን ከተጠያቂነት በፍጹም እንደማያመልጡ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
በተለያየ መልኩ በፓርቲያችን በከፍተኛ አመራሮች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ከወትሮው በብዙ እጥፍ በተጠናከረ መልኩ የማያንቀሳቅሱ እና ሰብዓዊ ነጻነትን የሚጋፉ፤ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥም የሚከቱ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች እና ለኢሕአፓ አመራሮች በተለያየ መንገድ የሚደርሷቸው ዛቻና ማስፈራሪያዎች የገዢው ፓርቲ አንዳንድ ሹማምንት ምን ያህል ሰላማዊ ትግልን እና ሰላማዊ ታጋዮችን እንደሚፈሩ እና እንደሚጠሉ ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ በዚህ ስርኣት መጠላት በትክክለኛ መንገድ ላይ ስለመሆናችን ማሳያ ነውና ያስጨንቅ የነበረው ለኢሕአፓ ውዴታ ቢኖራቸው ነበር፡፡
ይህ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ በህገ-መንግስቱ ጭምር የተሰጠውን የመሰብሰብ፣ የማደራጀት እና በሰላማዊ መንገድ የመታገል መብት ለመጠቀም በመራመዱ የሚደርስበት መሆኑ የሚያሳፍር ነው።
በተጨማሪም ይህንን ሁሉ የመብት ጥሰት የሚፈጽመው በየመድረኩ ስለዲሞክራሲ እና የመድብለ-ፓርቲ ስርኣት ሲደሰኩር የሚውለው ብልጽግና ፓርቲ መሆኑ ራሱኑ ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡
አንድ የመንግስት ከፍተኛ ሹም ስላልነበረበት እና በልጅነቱ ከስሚ ስሚ ውጭ ስለማያውቀው ‹የነጭ ሽብር› ታሪክ ከማንሳት ይልቅ እርሱና የሚያገለግለው መንግስቱ በየቦታው ስለሚጥዷቸው ጦርነቶች፣ ስለሚገፏቸው ሰብዓዊ መብቶች፣ በጅምላ በድሮን ስለሚጨፈጭፏቸው ንጹሃን፣ ወላጅ አልባ ስላደረጓቸው ህጻናት፣ ለስልጣናቸው ሲሉ ከበው ስለሚያስርቡት ሕዝብ፣ ስላስደፈሯቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፣ በየእስር ቤቱ ስላጎሯቸው ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች በጀመረ አፋቸው ለማውራት ቢችሉ መልካም ነበር፡፡
በነካ እጃቸው በትግራይ ስለፈጸሙት፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ላይ እየፈጸሙ ስላለው መከራ እና ግፍ ቢነግሩን ብለን እንጠብቃለን፡፡
ነገር ግን ገዢው ፓርቲ አሁን እየሄደ ባለው መንገድ አመራሮችን ዒላማ በማድረግ እና የፓርቲን ስም ያውም ከመንግስት አመራሮች በማይጠበቅ መልኩ በማጠልሸት እና በሀሰት በመወንጀል ኢሕአፓን ከሰላማዊ ትግል እንዲወጣ ማድረግ እንደማይቻል እናሳውቃለን።
ይልቁንም እንደዚህ አይነት አፈናዎች፣ ጭቆናዎች እና የመብት ረገጣዎች በፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰውን ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ያልሆነውን የህብረተሰብ ክፍልም የሚያማርሩ እና በጋራ ለመታገልም ዋና አነሳሽ ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከዛሬ በምናደርገው ትግል ውስጥ በቆራጥነት ከጎናችን በመቆም እየሰጠን ላለው ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ ልናመሰግን እንወዳለን፡፡ ከዚህ በኋላም በምናደርገው ጉዞ ይህ ድጋፍ እንደማይለየን ባለሙሉ እምነት ነን፡፡
ኢሕአፓ አሁን በያዘው መንገድ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ለመምራት እና ለዚህም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፊት ሆኖ ለመክፈል ያለውን ቁርጠኝነት ዛሬም በድጋሚ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያረጋግጣል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ታህሳስ 2 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ