ክልሎች በንፁሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቆም ካልቻሉ የፌደራሉ መንገስት ጣልቃ ገብቶ የሕግ የበላይነትን ሊያስጠብቅ ይገባሉ

ክልሎች በንፁሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቆም ካልቻሉ የፌደራሉ መንገስት ጣልቃ ገብቶ የሕግ የበላይነትን ሊያስጠብቅ ይገባሉ አሉ—ምሁራን

በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን ክልሎች ማስቆም እንዳለባቸዉና ያንን ማድረግ አቅም ከሌላቸዉ ግን የፌደራሉ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰዉ ሞት፤ መፈናቀልና አፈና ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተለመደ የመጣ ይመስላል፡፡
ምክንያቱም ዜጎች በነፃነት የመኖር ህልዉናቸዉን ተገፈዉ በተለይም ህጻናትና ሴቶች ለስቃይ ተዳርገዋል፡

የመተከል፣ የወለጋ እና የጉራ ፈርዳ አካባቢዎችም የንፁሃንን ሕይዎት መቀማታቸዉን የተያያዙት ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ተጠያቂ የሚያደርገዉ ኦነግ ሽኔንና ሌሎች የጥፋት ሃይሎችን ነዉ፡፡

ታዲያ ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት የእነዚህን አጥፊዎች ማንነት ማወቅ ከቻለ ስለምን እርምጃ ለመዉሰድ ክንዱ ዛለበት የሚለዉ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች ምክንያታቸዉ ምንድነዉ? መንግስትስ እንደ መንግስት የህግ የበላይነትን በምን መልኩ ማስከበር ይኖርበታል በሚለዉ ላይ ምሁራንን ጠይቋል፡፡

የጂግጂጋ ዩንቨርሲቲ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተርና መምህር አቶ ሰለሞን ጓዴ፣ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያት አንድም የሚመነጨዉ ከፖለቲካ ስርአት ነዉ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ መንግስት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ነዉ ይላሉ፡፡

ከፌደራሉ መንግስት ባለፈ ግጭት በሚነሳበት ክልል ዉስጥ ያለዉ አስተዳደር የዜጎችን መብት ማስጠበቅ ነበረበት ብለዋል፡፡

ክልሎች የዜጎችን የመኖር ነፃነት ማስጠበቅ እንዳለባቸዉ የሚያነሱት አቶ ሰለሞን ይህንን ማድረግ የሚያስችል አቅም ከሌላቸዉ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር-ቤት በሚፈቅደዉ መንገድ የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ማረጋጋት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፌደራልም ሆኑ የክልል አመራሮች ፅንፍ በመያዝ የሚያራምዱት ሃሳብ አገርን አንድ የሚደርግ ሳይሆን የሚለያይና ግጭት እንዲቀሰቀስ ስለሚያደርግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡

የመንግስት ትልቁ ሃላፊነትና ግዴታ የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሆነ የሚያነሱት ምሁሩ፤ ግጭቶች በተነሱ ቁጥር ኦነግ ሽኔና ትህነግ ነዉ እያሉ መቀጠል ተገቢ አይሆንም ብለዋል፡፡

የደብረ ታቦር ዩኝቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስና ሰብአዊ ፋካሊቲ ዲን የሆኑት አቶ ታምሩ በዛብህ በበኩላቸዉ፣የፀጥታ ስጋት ባለባቸዉ አካባቢዎች መንግስት አስቀድሞ መድረስ ነበረበት፤ ምክንያቱም የመንግስት ዋነኛዉ ተግባር የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡

አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚተላለፉ ስለመሆናቸዉ የሚያስረዱት ምሁሩ፤ አሁን ካለዉ መንግስት በተቃርኖ የሚቆሙ ሃይሎች ቢኖሩም ከክልል እና ከፌደራሉ መንግስት ዉጪ ሊሆኑ አይችሉም ነዉ የሚሉት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግን አሁን ኢትዮጵያ ከፊት ለፊቷ አገራዊ ምርጫ ይጠብቃታል፤ ለዚህ ደግሞ የዜጎች ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ እንደሆነ የሚያሰረዱት ምሁሩ የዜጎች ደህንነትና ነፃነት የማይጠበቅ ከሆነ ግን ምርጫዉ ላይ ሌላ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ባይ ናቸዉ፡፡

እናም ንፁሃን በተገደሉ ቁጥር የሃዘን መግለጫ ማዉጣት ብቻ ተገቢ ባለመሆኑ፣ የዜጎችን የመኖር ነፃነት የፌደራሉም ሆነ የክልል መንግስታት ተባብረዉ ማስቆም አለባቸዉ ሲል አጽንኦት ሰጥተዉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም