የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉን አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በእነ ዮሃንስ ቧያለው መዝገብ ስር የሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች፤ በግል ስልካቸው ያደረጓቸው የድምጽ ልውውጦች “ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጠለፉን” ጉዳያቸውን ለሚመለከተው ችሎት አስታወቁ። ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት የቀረበው የድምጽ ልውውጥ በህጉ መሰረት ስለመፈጸሙ እንዲረጋገጥላቸው አቤት ብለዋል።
በአማራ ክልል ካለው የጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በእነ አቶ ዮሃንስ ቧያለው መዝገብ ስር የሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች ብዛት 52 ተከሳሾች ነው። ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሰረተውን የሽብር ክስ ያስረዱልኛል በሚል የሰው ምስክሮች፣ የሰነድ ማስረጃ፣ የቪዲዮ፣ ኦዲዮ እና ሰነድ ማስረጃዎችን በፍላሽ ያካተተ “ገላጭ” እንዲሁም “የኤግዚቢት“ ማስረጃዎችን ጉዳዩን ለሚመለከተው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት አቅርቧል።
በተከሳሾቹ ላይ የቀረቡ የሰው ምስክሮችን ቃል አዳምጦ የጨረሰው ችሎቱ፤ ዐቃቤ ሕግ ባቀረባቸው በሰነድ ማስረጃዎች ላይ ተጠርጣሪዎቹ አስተያየት እንዲሰጡ ለዛሬ አርብ ጥር 8፤ 2018 ቀጥሮ ሰጥቶ ነበር። ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት ካቀረባቸው መካከል የተከሳሾች የስልክ ልውውጥ እንደሚገኝበት የጠቀሱት ተከሳሾቹ፤ የዜጎችን የግል ስልክ ልውውጥ መጥለፍ የሚቻለው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ መሆኑን ለችሎቱ ገልጸዋል።

ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ፋይል የመጨረሻ ገጽ ላይ፤ በማስረጃነት የተያያዘው የተከሳሾች የስልክ ግንኙነት ጠለፋ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትን በማስፈቀድ የተደረገ መሆኑን አመልክቷል። ጉዳዩን የሚመለከተው ችሎት ጠለፋው የተፈቀደበትን መዝገብ አስቀርቦ መመልከት እንደሚችልም በክስ ፋይሉ ላይ አስፍሯል።
ተከሳሾቹ በዛሬው ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ ግን የስልክ ጠለፋው “በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ስለመፈጸሙ እንዲረጋገጥላቸው” በጠበቆቻቸው አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ይህንኑ ጥያቄ አቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሃንስ በራሳቸው አንደበት ለችሎቱ አሰምተዋል። የስልክ ጠለፋው እንዲፈጸም ፍርድ ቤት ለዐቃቤ ሕግ የሰጠው ትዕዛዝ እንዲደርሳቸውም ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው በኩል ጠይቀዋል።
ጠበቆቹ ከዚህ በተጨማሪም በዐቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ተከሳሾቹ የሚያቀርቡት የጽሁፍ አስተያየት ተጠናቅቆ ለዛሬው ችሎት እንዳልደረሰላቸው ለችሎቱ ገልጸዋል። በመሆኑም የስልክ ጠለፋውን የተመለከተ ትዕዛዝ ሲደርሳቸው አንድ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ጥያቄው የቀረበለት የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ ተከሳሾቹ በሰነድ ማስረጃዎች ላይ የሚያዘጋጁትን አስተያየት ጥር 19፤ 2018 እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። የስልክ ጠለፋውን በተመለከተ ግን ትዕዛዝ በሚደርሳቸው ጊዜ ተከሳሾች አስተያየት እንደሚሰጡበት ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በዛሬው የችሎት ውሎ በእስር ላይ ከሚገኙት 16 ተከሳሾች ውስጥ አቶ ዮሃንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 11 ተከሳሾች በአካል ቀርበዋል። ከተከሳሾቹ ውስጥ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ የቀድሞው የኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና ዶ/ር ዘሪሁን ባህረው “በህመም” ምክንያት በችሎት አልተገኙም። አቶ አማረ መለስ የተባሉ ተከሳሽም ባጋጠማቸው “የአዕምሮ ህመም” ምክንያት ነው በችሎቱ በአካል ለመገኘት አለመቻላቸው ተገልጿል።
መሪጌታ በላይ አዳሙ የተባሉት ቀሪው ተከሳሽ፤ ፖሊስ የክህነት ልብሳቸውን ለብሰው እንዲሄዱ “ባለመፍቀዱ” ምክንያት መቅረታቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸን ለችሎቱ አስረድተዋል። ተከሳሹ የክህነት ልብሳቸውን ለብሰው በችሎት እንዲገኙ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በፍርድ ቤት የተፈቀደላቸው መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፤ በዚሁ አለባበስ ዛሬም ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ “ተዘጋጅተው” እያለ፤ ከፖሊስ ክልከላ እንደገጠማቸው አብራርተዋል።

የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎቱ፤ ተከሳሹ የክህነት ልብሳቸውን ለብሰው እንዲታደሙ በፍርድ ቤት ተፈቅዶላቸው እያለ ለምን ይህንን ትዕዛዝ እንዳልተፈጸመ ፖሊስ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል። በችሎቱ የተገኙት የማረሚያ ቤት ፖሊስ፤ ተከሳሹ የክህነት ልብሳቸውን ለብሰው ወደ ችሎት ያልመጡት የማረሚያ ቤቱ አመራሮች “አዲስ” በመሆናቸው ምክንያት “ስላልፈቀዱላቸው” መሆኑን አስረድተዋል።
ችሎቱም ፖሊስ ለተከሳሹ የተፈቀደላቸው የክህነት ልብስ ለብሶ ችሎት የመገኘት መብትን እንዲያከብር ትዕዛዝ በመስጠት የዛሬ ውሎውን አጠናቅቋል። በአቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ስር የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ 16 ተከሳሾች፤ በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሞልቷቸዋል። ጉዳያቸው በሌለበት ከሚታየው ተከሳሾች ውስጥ እስክንድር ነጋ እና ዘመነ ካሴ ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
