በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የወልቃይት-ጠገዴ-ሁመራ ዞን ሃላፊዎች በሰሜኑ ጦርነት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ረገድ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ወረደ ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠውልኛል አሉ።
አምባሳደሩ ትናንት በሁመራ ከተማ ጉብኝታቸው ወቅት፣ ከዚህ ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች ደኅንነታቸውን እና ክብራቸውን ባስጠበቀ መንገድ እና በቂ መረጃ ኖሯቸው በፍቃደኝነት ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ይገባል ማለታቸውን የአሜሪካ ኢምባሲ ዛሬ ካሠራጨው ንግግራቸው ሠምተናል።
አሜሪካ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
ኾኖም ተፈናቃዮችን የመመለሱን ሂደት በዋናነት መምራት ያለበት ፌደራል መንግሥቱ ነው ያሉት ማሲንጋ፣ የትግራይና አማራ ክልላዊ መንግሥታትም ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
አምባሳደሩ በሁመራ ቆይታቸው፣ ከዞኑ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።