የግብጹ የውሃና መስኖ ሚንስትር ሃኒ ስዋሊም፣ ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድቧ በግብጽ እና ሱዳን ላይ ላደረሠችው ጉዳት ካሳ መክፈል አለባት ሲሉ ለአገሪቱ ፓርላማ ተናገሩ።
ሚንስትሩ፣ ሕዳሴ ግድብ በናይል ወንዝ ላይ ግብጽ በዓመት ካላት የ55 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ድርሻ ላይ የ38 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ጉድለት አስከትሏል ማለታቸውን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል።
የግብጽ የውሃ ፍላጎት ባሁኑ ወቅት በዓመት 88 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ደርሷል ያሉት ሚንስትሩ፣ አገሪቱ ክፍተቱን ለመሙላት 23 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ላይ መኾኗን መግለጣቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል።