ሕወሃት፣ የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ሁመራ ላይ ያደረጉት ንግግር ተቸ።

ሕወሃት፣ የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ትናንት ሁመራ ላይ ያደረጉት ንግግር የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተፈራራሚ ወገኖች “ይበልጥ የሚያራራቅ” ነው በማለት ተቸ።

ሕወሃት፣ የትግራይን ሕዝብ ከወልቃይት እና ሁመራ አካባቢ ያፈናቀሉ ኃይሎች በሥልጣን ላይ እያሉ ተፈናቃዮች “ደኅንነታቸው ተጠብቆ” ሊመለሱ እና “እርቅ” እና “እውነተኛ ፖለቲካዊ አማራጭ” ሊኖር አይችልም ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አቋሙን ገልጧል።

አምባሳደሩ ፖለቲካን ወደ ጎን ገፋ በማድረግ ሕዝብን ማስቀደም ያስፈልጋል ማለታቸውን የተቸው ሕወሃት፣ የጦርነቱ ዋና ምክንያት “ፖለቲካዊ ቀውስ” መሆኑን መዘንጋት የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሸርሸር ነው በማለት ተችቷል።

“ገንቢ አስተዋጽኦ” ማድረግ በሚያስፈልግበት ባሁኑ ወቅት፣ ዓለማቀፍ አጋሮችን ጨምሮ ማንኛውም ወገን “ጠቃሚ ያልሆኑ” እና “አለመተማመንን” ሊያባብሱ የሚችሉ አስተያይቶች ባይሠጡ እንደሚመረጥም ሕወሃት አሳስቧል።