በኦሮሚያ ታጣቂዎች አንድ ምግብ ቤት በመግባት በፈጸሙት ጥቃት ሰዎችን መግደላቸው ተሰማ

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሰበ ቦሩ ወረዳ ሰቢቹ ቂንጣቢ በተባለ ቀበሌ ታጣቂዎች ባለፈው እሁድ ምሽት 4 ሰዓት ገደማ ወደ አንድ ምግብ ቤት በመግባት በፈጸሙት ጥቃት አንድ የ80 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በዚሁ ጥቃት፣ ሌሎች አምስት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሠባቸውና በአዶላ ዋዩ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መኾኑን ከወረዳው የመንግሥት ኃላፊዎች እና ከሌሎች ምንጮቹ መስማቱን የዜና ምንጩ ጠቅሷል።

ታጣቂዎቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ በአካባቢው ከሚገኝ ጫካ ገብተው መሠወራቸውንም ዘገባው አመልክቷል።

ጥቃቱን የፈጸሙት፣ የአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ናቸው በማለት የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል ተብሏል።