የሶማሊ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥምረት ተመሰረተ

አብዱራህማ ማህዲ የሚመሩት የኦብነግ ክንፍ፣ ‘ኮንግረስ ፎር ሶማሊ ኮዝ’ እና ‘ሶማሊ ሪጅናል ዴሞክራቲክ አሊያንስ’ የተባሉ ንቅናቄዎች “የሶማሊ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥምረት” የተባለ ስብስብ መሠረቱ።

አዲሱ ጥምረት፤ የሶማሊ ሕዝብን ፖለቲካዊ ውክልና ለማጠናከር ሲባል የተመሠረተ “የተቀናጀ” የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ እና ሲቪክ መድረክ መኾኑን ድርጅቶቹ ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ፣ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ሊሞከሩ የሚችሉ “የእርቅ” እና ‘ፍትሕ” መንገዶችን አሟጠው መጨረሳቸውንና የትዕግስት ዘመን ማብቃቱን ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠቅሠዋል።

የሶማሊ ሕዝብን መብት እና ክብር ለማስመለስ እና መጻኢ ዕድሉን ለማረጋገጥ ለትግል እንዲነሳ ጥሪ ያቀረቡት ድርጅቶቹ፣ ሌሎች ጭቆናን እና አገዛዝን ከሚቃወሙ አካላት ጋር በመርኅ ላይ የተመሠረተ አጋርነት ለመመስረት ዝግጁ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።