1 ቢሊየን ዶላር በመክፈል ሃገራት ቋሚ አባል የሚሆኑበት የትራምፕ “Board of Peace”
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ዳቮስ በሚገኙበት ወቅት የሰላም ቦርዱን ቻርተር በመፈረም ይፋ አድርገዋል።
የትራምፕ የሰላም ቦርድ አለም አቀፍ ግጭቶችን ይፈታል የተባለ አካል ሲሆን ሃገራት ይህንን ቦርድ በቋሚነት ለመቀላቀልም 1 ቢሊየን ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
ቦርዱ መጀመሪያ የመጣው በጋዛ ሰላም ለማምጣት የነበረ ቢሆንም ትራምፕ የቦርዱ ኃላፊነት ከጋዛ ባለፈ ሌሎች አለም አቀፍ ቀውሶችንም መፍታትን ያካትታል ብለዋል።
ትራምፕ በፊርማው ወቅት ” አንዴ ይህ ቦርድ ሙሉ ለሙሉ ከተመሰረተ፤ ማድረግ የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንችላለን። . . ተመድ ያለውን አቅም እንዳልተጠቀመ ሁሌ ስል ነበር፤ ተመድን ጨምሮ ከሌሎች አካላት ጋር እንሰራለን” ብለዋል።
ትራምፕ ቦርዱን በሊቀመንበርነት ሲመሩት ማርክ ሩቢዮ፣ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌርና የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋን ጨምሮ ሌሎችንም በውስጡ አካቷል።
ከ50-60 ሃገራት ቦርዱን እንዲቀላቀሉ ግብዣ ቀርቦላቸዋል ሲባል እስካሁን ግብጽ፣ ፓኪስታን፣ ጆርዳን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቱርኪዬ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር ፣ አርጀንቲናና ሌሎችም ግብዣውን መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
እስካሁን ቻይናና ህንድን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ለግብዣው ምላሽ አልሰጡም።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኔያሁ የትራምፕን ግብዣ መቀበላቸውን ገልጸዋል። ሩሲያ በበኩሏ አገዳ ከተጣለበት ሀብቷ 1 ቢሊየን ዶላር ፍልስጤማውያንን ለመርዳት ለቦርዱ እንደምትልክ አስታውቃለች።
ዘገባው የአልጄዚራ ነው።