” የትናንቱ ህወሓት ዛሬ የለችም ነገም አትመጣም ” – የህወሓት የቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ-መንበር

 

 

 

” የትናንቱ ህወሓት ዛሬ የለችም ነገም አትመጣም ” – የህወሓት የቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ነበር ተኽለብርሃን አርአያ

ነባር ታጋዩ በፓርቲው ውስጥ ከማእከላይ ኮሚቴ እስከ ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ለዓመታት በኃላፊነት ነበሩ።

ሐቀኛ ፣ ከሙስናና አድሎአዊ አሰራር የፀዱ ናቸው ተብለው በትግል ጎዶቻቸው የሚወደሱት ታጋዩ ከሁለት ዓመታት በፊት የተካሄደውንና የህወሓትን አመራር ለሁለት ቡድን ከፍሎ ክፉኛ ያዳከመው 14ኛ ጉባኤ ህገ-ወጥ ነው ብለው በመቋወም ፓርቲውንና ስልጣናቸውን ለቀዋል።

ታጋይ ተኽለብርሃን  አርአያ ጥር 6/2018 Landa Report ከተባለ ሚድያ ጋር ህወሓትን አስመልክተው በሰጡት ከአንድ ሰዓት በላይ ርዝማኔ ባለው ቃለ-መጠይቅ ምን አሉ ?

– ህወሓት በተለይ ከ1993 ዓ.ም የመሪነት መከፋፈል ወዲህ የዓላማ ጥራት ችግር ያጋጠመውና መዳከም የጀመረ ነው።

– ላለፉት 25 ዓመታት ሰብአዊ ሀብቱ  ( Social capital ) የበተነ ፓርቲ ነው።

– አመራር እና አባሉ በኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና መዘፈቅ ከጀመረ ቆይቷል።

– አዲስ ተተኪ ሀሳብ የሌለው ፤ በኔትወርክና ጥቅም የተሳሰረ ልል መሪነት ነው ያለው።

– የአሁኑ ህወሓት ስትራቴጂክ አመራር የለውም።

– ስትራቴጂክ አመራር የሌለው ፓርቲ ደሞ ፓርቲ ሆኖ አይቀጥልም።

– የግል ጥቅም እንጂ የአላማ አንድነት ያላሰባሰበው አመራር ቡድኖች እየፈጠረ አንዱ ሌላውን እያሳደደ እየበላ ፓርቲውን ወደ ማይድንበት ደረጃ አድርሶታል።

– ለ60 ቀናት ተሰብስበው ከመጨቃጨቅ ባሻገር የፈጠሩት የአስተሳሰብና የአመራር አንድነት አልነበረም።

– በመጨረሻ አንዱ ቡድን ሌላውን ቡድን ገፍትሮ ነሀሴ 2016 ዓ.ም ቁጥጥር ኮሚሽን ያልደገፈውና ያልተቀበለው ጉባኤ አካሄደ።

– ጉባኤው ህወሓት ወደ አራት ቡድን መከፋፈል ያዋለደ ነው።

– አንዱ ቡድን ስምረት ሌላው ወለዶ የሚባሉ ፓርቲዎች መስርቷል ፤ የተቀሩት ህወሓት ነን የሚሉት ደግሞ ለሁለት ቡድን ተከፍለው ውስጥ ለውስጥ እየተባሉ ነው።

– ደብረፅዮንና ጌታቸው ህወሓት በማዳከም ታሪክ ይጠይቃቸዋል።

– የትናንቱ ህወሓት ዛሬ የለችም ነገም አትመጣም።

– ዛሬ ያለው ህወሓት ስርዓትና መርህ አልባ ነው።

– ለአሁኑ መድረክ የሚዋጅ ህወሓት የለም።

– ስለ ግሉ ጥቅሙ እንጂ ስለ ህወሓት ጥንካሬ የሚጨነቅ አመራር የለም።

ትግራይ እንዴት ነው መዳን ያለባት ?

– የአሁኑ አጀንዳ ትግራይ እንዴት መዳን አለባት እንጂ ፤ ህወሓት እንዴት መዳን አለበት አይደለም መሆን የሚገባው።

– ውይይትን እና ስርዓት ማስቀደምን ያስፈልጋል።

– የተለያዩ አመለካከቶች የሚያስተናግድ አቋፊ መንግስት ማቋቋም ያስፈልጋል።

– የፓለቲካ የስህበት ማእከሉ ፓርቲዎች ሳይሆን መንግስት ስለ ማጠንከር መሆን አለበት።

– ምርጫ መካሄድና አለማካሄድ የህዝብ  እንጂ የፓርቲዎች መብት አይደለም።

– ህዝብ ለምርጫ ይዘጋጃል ፓርቲዎች የሚያወዳድራቸው ሀሳብና እጩ ያቀርባሉ።

– እኔ የሌለሁበት ምርጫ አይካሄድም የሚለው አይሰራም።

– ለምርጫ ምቹና አስቻይ ሁኔታ መፈጠር አለበት።

– ትግራይ በህዘብ ምርጫ የቆመ ስቪል መንግስትና አስተዳደር ያስፈልጋታል።