የአሜሪካ አምባሳደር በሁመራ ያደረጉት ጉብኝት “የዘር ማጥፋት” ወንጀል ከግምት ውስጥ አላስገባም ( ሕወሃት )

ሕወሃት፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ባለፈው ሳምንት በሁመራ ያደረጉት ጉብኝት እና ከጉብኝቱ በኋላ የሠጡት መግለጫ ከጦርነቱ ጀምሮ በአካባቢው የሚፈጸመውን “የዘር ማጥፋት” ወንጀል ከግምት ውስጥ አላስገባም ሲል ወቀሠ።

የአካባቢውን ተፈናቃዮች ደኅንነታቸውን ባስጠበቀ ኹኔታ የመመለስ ጉዳይ በሁለቱም ወገኖች ቅንጅትና እውቅና የሚካሄድ መኾን እንዳለበት የጠቀሠው ሕወሃት፣ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ መንግሥት መሪነት ተፈናቃዮች የመመለስ ሂደትን አሜሪካ እንደምትደግፍ መናገራቸው ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጭ ነው በማለት አዲስ ባስተላለፈው መልዕክት ተቃውሞውን ገልጧል።

ሕወሃት፣ አምባሳደር ማሲንጋ “ምዕራብ ትግራይ” የሚለውን የአካባቢውን ስያሜ በንግግራቸው እና መግለጫቸው አለመጠቀማቸው ትክክል አይደለም በማለት ጭምር ተችቷል። ሕወሃት አያይዞም፣ ሁመራ በምዕራብ ትግራይ የምትገኝ ከተማ መኾኗ ይታወቃል ብሏል።