(መሠረት ሚድያ)- የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ ማምሻውን ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተባለ የማህበራዊ ገፃቸው ላይ ኢትዮጵያን፣ ግብፅን እና የውሀ ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ አነጋጋሪ መረጃ አጋርተዋል።

መስከረም ወር ላይ የተመረቀው የህዳሴ ግድብ በአሜሪካ ፋይናንስ እንደተደረገ ከወራት በፊት ተናግረው የነበሩት ፕሬዝደንቱ በዛሬው ዕለት ለግብፁ ፕሬዝደንት አብደልፈታህ አልሲሲ በፃፉት ደብዳቤ ግብፅ በእስራኤል እና ሀማስ መሀል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረም ላደረገችው አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
“በግል ጓደኝነታችን እና አሜሪካ ለግብፅ ህዝብ ደህንነት ባላት ቁርጠኝነት ምክንያት በኢትዮጵያ እና ግብፅ መሀል የናይል ወንዝን በመጋራት ዙርያ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ድርድር ለማስጀመር ዝግጁ ነኝ” ያሉት ፕሬዝደንቱ የናይል ወንዝ ለግብፅ እና ለህዝቧ ያለውን ጥቅም አጥብቀው እንደሚረዱ ገልፀዋል።
አክለውም “ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የረዥም ግዜ የውሀ ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩ ልረዳችሁ እችላለሁ። በቀጠናው ያለ ማንኛውም ሀገር ብርቅዬ የሆነውን የናይል ወንዝ በብቸኝነት መቆጣጠር እንደማይችል እና ሌሎችን መጉዳት እንደማይችል አሜሪካ ታረጋግጣለች” በማለት ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ የተነገረለት መረጃ አጋርተዋል።
አሜሪካ በምትሳተፍበት እና ትክክለኛ በሆነ አካሄድ ተገማች የሆነ የውሀ ልቀት (በተለይ በድርቅ ወራት) ለግብፅ እና ሱዳን የሚኖርበት አሰራር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀይል የምታመነጭበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ትራምፕ በደብዳቤው ላይ አንስተዋል።
ትራምፕ ይህ ኢትዮጵያ የምታመነጨው ሀይል ለግብፅ እና ሱዳን የሚሰጥበት ወይም የሚሸጥበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በህዳሴ ግድብ ዙርያ በግብፅ እና ኢትዮጵያ መሀል ያለውን ውጥረት ማርገብ አሁን ላይ ትልቁ አጀንዳቸው መሆኑን አስፍረዋል። ይህ ደብዳቤ ለሳውዲ አረቢያው ንጉስ፣ ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝደንት፣ ለፕሬዝደንት ታዬ አፅቀስላሴ እና ለሱዳኑ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሀን በግልባጭ መላኩ ተገልጿል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን፣ ግብፅን እና ሱዳንን እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ ለማሸማገል ሙከራ ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ትረምፕ በመጀመርያው የፕሬዝደንትነት አስተዳደራቸው ዘመን የሶስቱን ሀገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሀ ሀብት ሚኒስትሮች በተደጋጋሚ በዋይት ሀውስ በማግኘት ቢያነጋግሩም መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻሉ ይታወሳል።
አሁን ላይ ትረምፕ የጋዛን ጉዳይ አስታከው ለግብፅ ውለታ ለመዋል እየተዘጋጁ እንደሆኑ ተንታኞች የጠቆሙ ሲሆን ይህም በቀጥታ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
-መሠረት ሚድያ-