የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የፖሊት ቢሮ ጥር 13 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛው ድርጅታዊ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳወች ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔወችን አሳልፏል። በዚህም መሠረት:-
፩) የድርጅቱ ስራ አመራር አባላት በተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ፖሊት ቢሮው አርበኛ እስክንድር ነጋ ያቀረበውን ማመልከቻ መርምሯል። በዚህም አርበኛ እስክንድር በግለሰባዊ ችግር ምክንያት ድርጅቱ በመደበበት የኃላፊነት ቦታ ላይ መቀጠል እንደማይችል ይልቁንም በድርጅት አባልነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን እና የሚጠበቅበትን ሀላፊነቶችና ግዴታዎች በሙሉ እንደሚፈፅም ጠቅሶ ያቀረበው ጥያቄ በነፃ ፈቃዱ እና ፍላጎቱ የቀረበ መሆኑን ፖሊት ቢሮው አረጋግጧል።
ሆኖም ግን ማመልከቻው ለፖሊት ቢሮው በደረሰበት ቅፅበት ለሚዲያ የወጣበት መንገድ የድርጅቱን አሰራር የሚጥስ እና ያልተገባ ትኩረት ለማግኘት የተደረገ መሆኑን ፖሊት ቢሮው ገምግሟል። ግለሰቡም ማመልከቻው ከአሰራር ውጭ በሚዲያ በኩል ይፋ መደረጉ ስህተት መሆኑን ላነጋገሩት የፖሊት ቢሮ አባላት አሳውቋል። እንዲሁም የድርጅታችን ምስረታ ይፋ በሆነ ማግስት እጅግ አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉ ይህ ጥያቄ መቅረቡ ግዜውን የጠበቀ አለመሆኑን አምኖበት በቃል ይቅርታ ጠይቋል።
በመሆኑም አሳማኝ ምክንያቶች ካሉም እንኳን ትክክለኛውን ጊዜ መጠበቅ ሲገባው ከሌሎች አስቸኳይ የህልውና አጀንዳ በላይ ይህ ጉዳይ የድርጅቱ የመጀመሪያ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ፖሊት ቢሮውን ያሳዘነው ቢሆንም ግለሰቡ በአባልነት ብቻ ለመቀጠል ያቀረበውን ማመልከቻ ፖሊት ቢሮው ተቀብሎታል። ፖሊት ቢሮዉ ለአርበኛ እስክንድር ተሰጥቶ በነበረው የኃላፊነት ቦታ ላይ ሌላ ሰው የሚተካ ይሆናል።
፪) የወለጋ ክፍለ ሀገር ፋኖ እዝ (ቢዛሞ) የድርጅቱ መዋቅር አካል የሚሆኑበትን ሁኔታ ላይ ውሳኔ ተላልፏል። እዙ በድርጅቱ ውስጥ የጠቅላላ ጉባኤ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የስራ አስፈፃሚ እንዲሁም ሌሎች መዋቅሮች ውስጥ ተመጣጣኝ እና አስፈላጊ ውክልና እንዲኖረው ወስኗል።
፫) በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በተጠቀሰው መሠረት የአባት አርበኞች ምክር ቤት መዋቅር እንዲቋቋም ውሳኔ ተላልፏል። ዝርዝር ጉዳዩን በቀጣይ የምናሳውቅ ይሆናል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ