ለሰፊው የአማራ ሕዝብ መብትና ሕልውና መረጋገጥ ሲባል የመጨረሻው መጀመሪያ ትግል ይደረግ ዘንድ አንድ አማራዊ ድርጅት ተመስርቷል! የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ምስረታን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የምስራች!

ለሰፊው የአማራ ሕዝብ መብትና ሕልውና መረጋገጥ ሲባል የመጨረሻው መጀመሪያ ትግል ይደረግ ዘንድ አንድ አማራዊ ድርጅት ተመስርቷል!

አፋብኃና አፋህድ እራሳቸውን አክስመው በዘላቂነት የአማራ ሕዝብን ሊወክል የሚችል አንድ ወጥ አደረጃጀት በመፍጠርና ስያሜውንም “አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ” በሚል ዛሬ ጥር 09/2018 ዓ/ም በይፋ መመስረታቸውን በአዲሱ ሕዝብ ግንኙነታቸው መምሪያ በኩል በላኩት መግለጫ አሳውቀዋል።

አማራን ከፈፅሞ ጥፋት መታደግና ፍትሓዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ( ፍትሕ ርትዕ ማስፈን) እንዲሁም በዘላቂነት ለመወከል እና ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኃይሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከመፍረስ ታድጎ ክብሯንና ልዕልናዋን አስጠብቆ እንደ ሀገር እንዲያስቀጥል ተደርጎ የተዋቀረው ” የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ /አፋብን/ ዛሬ ጥር 09/2018 ዓ/ም መመስረቱ ነው የታወቀ። መግለጫውን አንብቡት ……………..

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ምስረታን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ጥር 09 2018

እነሆ ዛሬ ጥር 09 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያን እና ቀጠናውን የሚያተራምሰው የብልፅግና ቡድን እስትንፋስ የሚፈልቅበትን ሸለቆ የሚዘጋ ታሪካዊ ውሳኔ ወስነናል። ጓዶቻችን ለከፈሉት መስዋዕትነት የሚመጥን ተልዕኮን መከወን ግዴታችን የሆነ እኛ የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች አመራሮች የአብይ አህመድ የስልጣን እድሜ የሚበቅልበትን ንቃቃት በፍፁም ወንድማማችነት እና አንድነት ደፍነነዋል። የአማራ ትግል አንድ ይሆን ዘንድ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት አመራሮች ድፍረትን፣ ሆደ ሰፊነትን፣ ቆራጥነትን እና ለህዝብ መታመንን በሚጠይቀው ታሪካዊ ውሳኔያችን የፋኖን አንድነት እውን ማድረግ ችለናል። ለመላው የአማራ ህዝብ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጲያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያለን‼️ አንድ መሪ፣ አንድ ድርጅት ሰይመናል።
አሁን ወደ ስትራቴጅካዊ ግባችን የሚወስደን ምእራፍ ወለል ብሎ ተከፍቷል። ሜዳውም ፈረሱም በእጃችን ሆኗል።
እንደ ብዙዎቹ ነባር የዓለም ስልጣኔወች ሁሉ ለረጅም ዘመናት በታሪካዊ መሰናክሎች ያልተደናቀፈ ቅብብሎሽ ያለው የግርማዊ ትላንት የታሪክ ባለቤት የሆነው የአማራ ሕዝብ እንዲሁም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቶዎች ለሚበልጡ ዓመታት በተለይም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ የስልጣኔ ግጭት በወለደው የትውልዶች ጦርነት እየተፈተኑ ይገኛሉ። በዘመናዊው ታሪካችን በቀጥታ አማራን ዒላማ ያደረገው ተከታታይ ዘመቻ በውስጣዊ ድክመቶቻችን ታግዞ ሁሉንም ህዝቦች በተገቢው መልኩ አሳታፊ ባልሆኑ የአሸናፊዎች ስርአት ሀገራችን ያልተረጋጋና እና የመፍረስ ስጋት ያለባት ሀገረ መንግስት ሲያደርግ ህዝባችንንም ለከፋ የመጥፋት (ህልውና) አደጋ አጋልጦታል። ይህንን በራሳችን ወገኖች ኢትዮጵያዊያን ባለቤትነትና ቅጥረኝነት የሚመራ ውስብስብ ሀገራዊ እና ህዝባዊ አደጋ ለመረዳት እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ብሎም መፍትሔ ለማበጀት ብዙ ማገዶ ፈጅቷል።

የአማራ ሕዝብ ራሱን በመዘንጋትና ሀገሩን በማስቀደም እየኖረ በራሱም ሆነ በሀገሩ ላይ የተፈጠረውን ታላቅ ተቃርኖ በጊዜው ባለመረዳቱ ራሱን ያገኘው ሀገሩን ተነጥቆ ሀገር አልባ ሆኖ እንዲሁም መንግስት መር በሆነ የዘር ማጥፋት በከፋ የመጥፋት አደጋ ውስጥ ሆኖ ነው። በእርግጥ አማራው በመጥፋት ላይ ያለ ህዝብ ነው። ይህንን ህዝባዊ አደጋ ለመቀልበስ ብሎም ሁለንተናዊ ህዝባዊ ጥቅሞቹን ለማስከበርና አዲስ ስልጣኔ ለመገንባት አዲስ አማራዊ አብዮት በማካሄድ ላይ እንገኛለን። የዚህ ህዝባዊ ቁጣ መነሻ ምክንያት የህልውና አደጋው ቢሆንም አደጋውን ከመቀልበስ ባሻገር ግዙፍ ራዕይ የቀነበበ ህዝባዊና ሀገራዊ እንዲሁም ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ መሻቶችን ቀርጿል።
የአዲሱ የአማራ ልሂቅ ራስ ጠል ዕሳቤ እና ባህል፣ የህዝባችን ፖለቲካዊ ድብታ እና ራስን ማግለል፣ በጥገኝነት በራስ ህዝብ ላይ የመቆመር ዝንባሌ፣ ያልተደራጀ እና የማይተመማን ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መፈጠር፣ በጠላት ፍላጎት ልክ የተቀረጹ መጥፎ ኤሊቶች የስልጣን ወንበር ይዘው አማራን እንዳይደራጅ መከልከል/መከላከል እንደ ህዝብ የመጥፋትን ስጋት ላስከተለ የህልውና አደጋ አጋልጠውናል።
ይህን የገጠመንን እንደ ህዝብ የመጥፋት አደጋ ለመቀልበስ ስንነሳ ብሎም ለብዙ አስርት አመታት ያጣነውን በራስ ሀሳብ መደራጀት ማስመለስ ተከትሎ ከመጥፋት ለመዳን የሚያስችለንን ትግል ማድረግ ችለናል። ትግሉም ስደተኛውን ፖለቲካችንን ህዝባዊ በሆነ ዕሳቤ እና አደረጃጀት መሬት ላይ በመተከሉም ሊጸና ችሏል።
እንደ ማህበረሰብ ያጋጠመን ውስጣዊ የመበስበስ አደጋ ትግሉ በተፈለገው ፍጥነት እንዳያድግ እና ወደ ስትራቴጂካዊ አሸናፊነት እንዳያመራ በእጅጉ ፈትነውናል፡፡ ጠላቶቻችን በየጊዜው የተቃርኖ ቅኝትን ወደ ውስጥ በማስረግ ብሔራዊ አንድነታችንን ፈትነውታል። ይሁንና አዲሱ ትውልድ በፍጹም ብሔራዊ ቁጭት በመነሳት ይህን ፈተና በጀግንነት ተጋፍጦታል። አሸንፏልም። በዚህም ከውድቀት የሚነሳበትን እና ከልዩነት ግርዶሽ ወደ በብሔራዊ አንድነት በመሻገር ህዝባዊ አሸናፊነት የሚያረጋግጥበትን ብሔራዊ ንቃት ተጠቅሞ የአደረጃጀት አንድነትን በትግል ለማሳካት ችሏል።
ባለፉት ጊዜያት ባልተማከለ አደረጃጀት በቁርጠኝነት በተከፈለው የህይወት መስዋዕትነት የተገኙ ድሎች የአገዛዙ የስልጣን ምንጭ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት በማፈራረስ አገዛዙን ተራ የአራት ኪሎ ሸማቂ እንዲሆን አድርገነዋል፡፡ ትግሉ ያልተማከለ አደረጃጀት ስልትን መጠቀሙ ተለዋዋጭ እና ለአገዛዙ እንዳይመች በማድረግ በአጭር ጊዜ አገዛዙን በማያንሰራራበት ደረጃ ማዳከም ተችሏል፡፡ የአገዛዙን ጀነራሎች የጦር አዛዥነታቸውን እረስተው ምላሳቸው ብቻ የቀራቸው ተራ ካድሪዎች አድርገናቸዋል፡፡ የትግሉ መጀመሪያው ምዕራፍ በድል በመጠናቀቁ የአገዛዙ ሰራዊት በመፈራረሱ ፋኖ ወደ ተተኪ ሰራዊትነት ማደግ ስላለበት እና ፖለቲካውን አደራጅቶ መምራት በማስፈለጉ አንድ የፋኖ አደረጃጀት ለመፍጠር በተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በሂደቱም የትግሉ የዕድገት ደረጃ የራሱን ድርሻ የሚወስድ ቢሆንም ነባር የተቃርኖ ቅኝቶች እና ሰራጊ የፍላጎት ቡድኖች ጣልቃ ገብነት እና መርዛማ የጠላት እጆች ዋና ፈተናዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮችን ተቋቁመን በዚህ የተባረከ ቀን ዛሬ የአንድነት ሪቫን ተቆርጧል።ፋኖ አንድ ሆኗል።
በድጋሜ እንኳን ደስ ያለን‼️
በዚህ የአደረጃጀት አንድነት የአማራ ትግል ነባር እና ብልሹ ራስ ጠል እና በታኝ ዕሳቤ እና አሰላለፎችን አሸንፏል። ጎታች ከሆኑ አሰላለፎች በመላቀቅ የውድቀትን ረግረግ በብሔራዊ ንቃቱ ተሻግሯል። በሠራዊቱ እና በደጀኑ ህዝብ ውስጥ ሲብሰለሰል የኖረውን ጥያቄ መልሷል፡፡ በአማራ አንድነት ላይ የነበሩ የተሳሳቱ እና አሉታዊ ምልከታዎችን አርሟል።
ዛሬ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)/ሲመሰረት በቀደሙ የአደረጃጀት አንድነት የማምጣት ሂደት ወቅት የታዩ ድክመቶች እና ክፍተቶችን በማረም እንዲሁም የሁሉንም ባለድርሻዎች ተሳትፎ እና ትምምን በመፍጠር ጭምር ነው። ይህ ውህድ ድርጅት የአላማ እና የአስተሳሰብ አንድነት ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህም ድርጅታችን የሚመራበት ርዕዮተ አለም “የአማራ ብሔርተኝነት” ሲሆን ይህም የወቅቱን የህልውና ትግል ከማሸነፍ ጀምሮ በዘላቂነት የህዝቡን ህልውና እንዲሁም ማንነቱን በማረጋገጥ መብት እና ጥቅሞቹን ለማስከበር የምንታገልበት የአስተሳሰብ ቅኝት ይሆናል። የአማራ ብሔርተኝነት በራስ በቅነት ሁለንተናዊ ውስጣዊ አቅምን በመገንባት በሀገራዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ የህዝባችንን ህልውና በማረጋገጥ መብት እና ጥቅሞቹን በማስጠበቅ የሌሎች ኢትዮጵያውያን የቡድን እና የግለሰብ መብቶች የሚከበርበት ስርዓት በማንበር በፍትሀዊ እና ሰላማዊ አብሮነት የሀገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚተጋ ነው።
በርካታ ቀናትን በወሰደ ጥልቅ ፖለቲካዊ ውይይቶች፣ ቅንነትን እና ወንድማማችነትን ያስቀደመው የድርጅት ምስረታ ሂደት በርካታ ምዕራፎችን ያለፈ ነው። የመግባቢያ ቃል ኪዳን ሰነድን በመፈራረም የተጀመረው ሂደት የድርጅቱን መመስረቻ ሰነድ (ሕገ ደንብ) በማፅደቅ እና ከፍተኛ አመራሩን በመሰየም በስኬት ተጠናቋል። በዚህም መሰረት

አርበኛ ዘመነ ካሴ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር፤ አርበኛ መከታው ማሞ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፤ አርበኛ ሐብቴ ወልዴ ምክትል ሊቀመንበር ለወታደራዊ ጉዳዮች፤ አርበኛ ሔኖክ አዲሴ ምክትል ሊቀመንበር ለፖለቲካዊ ጉዳዮች በማድረግ ሰይሟል።
እንዲሁም የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ከታች ለተዘረዘሩት መምሪያዎች አመራሮችን መድቧል፦
ወታደራዊ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ
ም/ወታደራዊ አዛዥ – አርበኛ ምሬ ወዳጆ
ም/አዛዥ ለወ/አስተዳደር – አርበኛ ዝናቡ ልንገረው
ወ/ስልጠና መምሪያ – አርበኛ ሳሙኤል ባለዕድል
ልዩ ዘመቻ – አርበኛ ድርሳን ብርሀኔ
ዘመቻ መምሪያ – አርበኛ ባዩ አለባቸው
ፖለቲካ መምሪያ – አርበኛ ጌታ አስራዳ
አደረጃጀት መምሪያ – አርበኛ ምንተስኖት ወንድአፈራሁ
ድርጅት ጽ/ቤት – አርበኛ አስቻለው በለጠ
የህዝብ ግንኙነት – አርበኛ አስረስ ማረ ዳምጤ
የህዝብ አስተዳደር መምሪያ – አርበኛ ዘመነ ምህረት
ፋይናንስ እና ግዢ አስተዳደር – አርበኛ አሻግሬ ባዬ
ፖሊሲ እና ስትራቴጂ – አርበኛ እስክንድር ነጋ
አጋርነት እና ትብብር – አርበኛ አበበ ፈንታው
የውጭ ጉዳይ መምሪያ – አርበኛ ብሩክ ስለሺ

በዚህ ታሪካዊ እለት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ቀጣዮችን መልዕክቶች ያቀርባል።

፩) መልዕክት ለድርጅታችን ሠራዊት፦

ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈልክበት ያለው ትግል ፍሬ እንዲያፈራ እና የተሟላ አሸናፊነት እንዲረጋገጥ የአደረጃጀት አንድነት የግድ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተነሳው ሀሳብ ተገቢውን መልስ አግኝቶ የፋኖ አንድነት ተበስሯል። ይህ ትልቅ የምስራች የሚያስገኘውን ተጨማሪ አቅም በመጠቀም በጽናት እና ቁርጠኝነት ትግሉን እንድትቀጥል ጥሪ እናቀርባለን። በትግል ሂደት አዲሱ ትውልድ በብሔራዊ ቁጭት እና ንቃት ያገኘውን የአስተሳሰብ አቅም በመጠቀም ውስጣዊ ትግል የሚፈልጉ ነባር ዕክሎችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መታገል እንዲቀጥል እያሳሰብን የድርጅት ውህደትን ተከትሎ ለሚመጡ የመዋቅር እና የአሰራር ማሻሻያዎች ተገቢውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በቅንነት መተባበር አስፈላጊ እንደሆነ እንገልፃለን። በተጨማሪም በየደረጃው ያለው መዋቅር ለቀጣይ ግዳጆች የሚያስፈልገው ወትሮ ዝግጁነት እንዲያረጋግጥ በጥብቅ እናሳስባለን።

፪) መልዕክት ለህዝባችን ፦

የትግሉ ደጀን የሆነው ህዝባችን በመድረኮች ሲያቀርብ ለነበረው የአንድነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን በድጋሚ እያበሰርን እስካሁን ትግሉን በባለቤትነት በመውሰድ በትዕግስት የድርሻውን ሀላፊነት ወስዶ የፈጸመውን ትልቅ ብሔራዊ ጀብድ የአንድነትን ጉልበት ተጠቅሞ አንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን።

፫) መልዕክት ለአማራ ዲያስፖራ፦

በተለያዩ የአለም ክፍል የሚገኘው የአማራ ዲያስፖራ በትግሉ መጀመሪያ ወቅት ሲያደርገው የነበረው የነቃ ተሳትፎ በሂደት በተፈጠሩ የአመለካከት መዛነፎች እና ጣልቃ ገብነቶች በተለይም የአደረጃጀት አንድነት ባለመምጣቱ ምክንያት በነበረው ግለት አለመቀጠሉን እና አቅሙን ተጠቅሞ ትግሉን በሚገባው መልክ ማገዝ አለመቻሉን አስተውለናል። ሆኖም ሠራዊቱ ፣ ህዝቡ እና አብዛኛው ዲያስፖራው በጉጉት ሲጠብቀው የቆየው የፋኖ አንድነት ተጠናቆ ውህድ ድርጅት ለመመስረት በቅቷል። በዚህም እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን ለቀጣዩ የትግል ምዕራፍ ከእናንተ የሚጠበቀውን ድጋፍ ለማድረግ እንዲያስችል በራስ ተነሳሽነት የአደረጃጀት አንድነት ከመፍጠር በተጨማሪም ትግሉን አስመልክቶ ከድርጅታችን የሚሰጡ አቅጣጫ እና መመሪያዎችን በቅንነት እንድትተገብሩ ከወዲሁ እናሳስባለን።

፬) መልዕክት በጸረ አገዛዝ የትግል መስመር ላሉ ብሔራዊ የትግል ሀይሎች እና የማህበረሰብ ክፍል፦

ሃገራችን አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ በይፋ የዘር ፍጅት ያልታወጀበት እና የህልውና አደጋ ያላንዣበበት ኢትዮጲያዊ ወገን አለ ብለን አናምንም። ሁሉም ህዝብ ህልውናው አደጋ ውስጥ ነው። ኢትዮጲያ የገደል ጠርዝ ላይ ናት። በመሆኑም የፋኖ ትግል ለአማራ ህዝብ ህልውናና ለሌሎች ኢትዮጲያውያን ወገኖችም ጭምር ፖለቲካዊ መዳን ወሳኝ መፍትሄ ያዘለ ነው። የአማራ ድል ለጉራጌውም፥ ለትግሬውም፥ ለኦሮሞውም፥ ለጉምዙም፥ ለአፋሩም፥ ለሶማሌውም፥ ለወላይታውም፥ ለሲዳማውም፥ ለጋሞው እና ለሌሎችም ህዝቦች ድል ነው። በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ልሂቃን በጋራ በመቆም ለጋራ እጣ ፋንታ መታገል ይኖርባቸዋል። የዳር ተመልካች መሆን ለወረፋ ጥቃትና ጥፋት ይዳርጋልና።
አብይ የአፍሪካ ቀንድ ሹል ቀንድ ነው። ሁሉንም እየወጋ ሁሉንም እያደማ ነው። ሁሉንም የቀጠናው ህዝቦች ቤት በእጁም በእግሩም እየረበሼ ነው። ስለሆነም ዘር አጥፊውን የአብይ አህመድ አገዛዝ ለማስወገድ ኢትዮጲያውያን ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ የቀጠናው ሃይሎች መተባበር አለባቸው። ይህን አገዛዝ ለማስወገድና ቀጠናውን ለማረጋጋት የሚደረጉ ትብብሮች በሙሉ ልክ ናቸው። የቀጠናው ህዝቦች ረፍትና ልማት ይሻሉ።ይገባቼውማል።
አረመኔው አገዛዝ የሚከተለው ከፋፍሎ የማጥቃት እና የማስጠቃት ስልት ጊዚያዊ የስልጣን ዕፎይታ የፈጠረለት ቢሆንም ይህንን በመገንዘብ በትብብር አገዛዙን በማስወገድ ላይ የታዩ መግባባቶችን ማሳደግ እና የአገዛዙን ዕድሜ ማሳጠር አስፈላጊ ነው። ለዚህም የፋኖ አንድነት የፈጠረውን ተጨማሪ አቅም እና ዕድል እንዲሁም በእስካሁኑ ሂደት በጸረ አገዛዝ ትግል አስፈላጊነት ላይ የታዩ መግባባቶች የተሟላ በማቀናጀት የዘር ማጥፋት ጦርነት ከመመከት ወደ ስትራቴጂካዊ ማጥቃት በመቀየር አገዛዙን ለማስወገድ እንድንሰራ ጥሪ እናቀርባለን።

፭) መልዕክት ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ፦

አብይ አህመድ መሩ የብልጽግና አገዛዝ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ላሉት ወደ ስምንት ለሚጠጉ አመታት በህዝቦች ላይ ከፍተኛ እልቂት መፈጸሙ እንደሚታወቅ እሙን ነው። አገዛዙ ሀገሪቱን የማያባራ ጦርነት ውስጥ በማስገባት በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ሰብአዊ ውድመት፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀት እና ማህበራዊ ቀውስን አስከትሏል። ይህ አገዛዝ ጸረ ህዝብ በመሆኑ ችግሩ የማይታከም፣ ከስህተቱ የማይማር እና አንዳች ተአማኒነት ያልታየበትም ነው። የአገዛዙ የጦረኝነት ባህሪ ከኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግርነት አልፎ ቀጠናዊ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ተጨባጭ አደጋ ከፈጠረ ውሎ አድሯል። አገዛዙ በአማራ ህዝብ ላይ ያወጀው የዘር ማጥፋት ጦርነት እና የተከሰተው የህልውና አደጋ ጦርነቱን ከመቀልበስ ውጭ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ፋኖ በህዝባዊ የትግል መስመር አገዛዙን ላለፉት 30 ወራት እየታገለም ይገኛል። ከፋኖም በተጨማሪ ሌሎች ጸረ አገዛዝ ብሔራዊ ሀይሎች በዚህ ህዝባዊ የትግል መስመር ውስጥ የህዝባቸውን ህልውና ለማረጋገጥ በትግል ላይ ይገኛሉ።
ይህን ህዝባዊ፣ ሀገራዊ ብሎም ቀጠናዊ አደጋ ማስወገድ እና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ብሎም ተራዛሚ ቀጠናዊ ጦርነቶችን ማስወገድ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም እናምናለን። ከዚህም በመነሳት ጸረ ህዝብ እና ጸረ ሰላም ለሆነው የብልጽግና ሀይል የሚደረገውን ድጋፍ በማቆም እንዲሁም አስፈላጊውን ጫና በማድረግ የአገዛዙን የጥፋት አቅም በማሳጣት እንድትተባበሩ ጥሪ እናቀርባለን። በተጨማሪም የፋኖን እና የሌሎችን የጸረ አገዛዝ ትግል የሚያደርጉ ሀይሎችን ትብብር በተቻለው አቅም እንድትደግፉ ጥሪ እናቀርባለን። የዕርዳታ ድርጅቶችም በጦርነቱ ለተጎዳው ህዝባችን አስፈላጊውን ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስለት የሚቻለውን

እንድታደርጉ ጥሪ እያቀረብን በእኛ በኩል አስፈላጊውን ትብብር እንደምናደርግ ልናሳውቅ እንወዳለን።

፮) መልዕክት ለመለዮ ለባሹና ሚሊሻ

የአገዛዙ የስልጣን ምንጭ ህዝብ ሳይሆን የመለዮ ለባሾች ደም እንደሆነ ለእናንተ የተሰወረ አይደለም፡፡ አገዛዙ የስልጣን እድሜውን እስካራዘመለት ድረስ ለህይዎታችሁ ደንታ የሌለው መሆኑም ከእናንተ የተሰወረ አይደለም፡፡ የፋኖ ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተከብሮ የሚኖርባት ሀገር መገንባት፣ የእናንተ መለዮ ለባሾች ደህንነት እና ክብር ተጠብቆ ሀገራችሁን እንድታገለግሉ የምትከፍሉት የህይወት መስዋዕትነትም ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ሞታችሁ ለሀገራችሁ ሳይሆን ለአንድ በሰው ደም ለማይጠረቃ አገዛዝ መሆኑን ተረድታችሁ ወደ ፋኖ ትግል እንድትቀላቀሉ ጥሪ እያቀረብን ሙሉ መዋቅራችን ከመቼውም ጊዜ በተለዬ እናንተን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ለድርጅታችን ሞስረታ ስኬት ለተጉ ሁሉ የላቅ ክብር ያለው መሆኑን እየገለጽን በተለይም ፦

1) ለመላው የአማራ ህዝብና ለሃገር ወዳድ ኢትዮጲያውያን፤ ለማይቋረጠው ልባዊ ድጋፋችሁና ለምክራችሁ፥ ለግሳፂያችሁ እናመሰግናለን። ልፋታችሁ ይህን አንድነት ወልዷል።

2) ለመላው ፋኖ አባላት፤ ለፍፁም ንፁህ ጓዳዊ ግፊታችሁ እና አንድነት ናፋቂነታችሁ እናመሰግናለን። የእናንተ የቀን ከሌት ጉትጎታና ውትወታ ባይኖር ሰንፈን የምንዝል አንታጣም ነበር። ደማችሁም ግፊታችሁም አንድነቱን ወልዷል።

3) ለመላው የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች፤ በተለይ በዚህኛው የአንድነት ሂደት ላሳያችሁት አመራርና ቁርጠኝነት ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል።
በተለይ የአንድነት ሂደቱን ያሳለጣችሁ የሁለቱ ድርጅቶች የቴክኒካል ኮሚቴ አባላት እጅግ ታላቅ ክብር ይገባችኋል። ያሳያችሁት የአመራር ብቃት፥ ጥበብና መፍትሄ አፍላቂነት ልዩ ነበር።

4) ሂደቱን ለታዘቡ ሽማግሌዎች፤ በልኡል አስፋወሰን አስራተ ካሳ የሚመራው አምባሳደር ብ/መስቀል ነጋ እና ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ሰባት አባላትን ያካታተው የታዛቢወች ቡድን ሂደቱን በገለልተኛነት በመከታተል ፣ ቴክኒካል ኮሚቴው በጠየቃቸው ጊዜ ሁሉ የመፈትሔ ሀሳብ በማቅረብ ላደረጉት አስተዋጽኦ ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን።

በመጨረሻም ድርጅቱን ለማዋለድ ከተከፈለው መስዋዕትነት ባልተናነሰ ድርጅቱን በዘላቂነት ለማጽናት የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለማሸነፍ ከላይ የተጠቀሳችሁ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ገንቢ ሚና እንድትጫወጡ ታሪካዊ ጥሪ እናቀርባለን።