ግንቦት 7 ለኢትዮጵያዊነት ቆሚያለሁ የሚለን የምሩን ወይስ ድራማ እየሰራብን? #ግርማክሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

እሁድ የካቲት 10 ቀን 2011፣ ግንቦት ሰባት በደብረ ማርቆስ ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባ አድርጓል። ስብሰባው የተሳካ ስብሰባ እንደነበረ ነው ደብረ ማርቆስ ነዋሪ ከነበሩ የደረሰኝ መረጃ የሚገልጸው። የተለቀቁ ፎቶዎችም ይሄንን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።

አንዳንድ ጽንፈኛ ቤተ አማራዎች የደብረ ማርቆስ ህዝብ ላይ፣ “ለምን ግንቦት ሰባትን ደገፋችሁ ?” በሚል ነው መሰለኝ ጣት ለመቀሰር የሞከሩም አሉ። ይህ ማሳዘን ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው። የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ፣ ማን እንደሆነ፣ አገር ሁሉ የሚያውቀው ነው። “የኛን የአማራነት ፖለቲካ ለምን አልተቀበለም ?” ብሎ አፍላፊ መካፈት ትርፉ መላላጥ ነው።

ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ጽፊያለሁ። የአማራ ወይንም አማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄረተኛው ፣ በትግራይና ኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት፣ እንደ ጠላት እየታየ፣ ተለይቶ ሲጠቃና ሲገለል ነበር። አሁንም እንደተገለለ ነው። ከዚህም የተነሳ፣ “ራሳችንን መከላከል ስላለብን ፣ የሕልዉና ጉዳይ ነው” በሚል እንደ አብን ያሉ በአማራነት ስም ተደራጅተዋል። መደራጀታቸውን ባልደግፈውም፣ እንደማልቃወም፣ ለምን እንደተደራጁም እንደምረዳ በመግለጽ፣ በሂደት ግን ከአማራነት አልፈው አድማሳቸውን ካላሰፉ በቀር ለጊዜው ድጋፍ ቢያገኙም፣ ብዙ ዘልቀው መሄድ እንደማይችሉ መክሪያለሁ።

ሆኖም የአማራ ድርጅቶች “አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ” የሚል አግላይ መፈክር እያነገቡ፣ ውስጣችን አለ የሚሉትን ኢትዮጵያዊነትን ከማጉላት ይልቅ፣ አማራነትን ብቻ ማጉላታቸው ለብዙ ወገኖች፣ እኔንም ጨምሮ ምቾት አልሰጠም።

የደብረ ማርቆሱ ሰልፍ እንደ አብን ላሉ ድርጅቶች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሰልፍ ነው። አንደኛ ከአማራ ድርጅቶች ሕዝቡ፣ “አማራ ተበደለ” ከማለትና ብሶት ከማሰማት ውጭ ግልጽ አማራጭ አልቀረበለትም። ሕዝቡን የሚመጥን፣ ወደፊት የሚያሻግር፣ መግለጫ ከማውጣት ያለፈ፣ መፍትሄዎችን የሚያስቀምጥ አማራጮችን ማቅረብ መጀመር አለባቸው። ሁለተኛ ኢትዮጵያዊነት ማጉላት መጀመር አለባቸው። መግለጫዎቻቸው ራሱ ‘አማራ” የሚል እንጂ “ኢትዮጵያ” የሚል ብዙ አይነበብበትም። ያስ መስተካከl መቻል አለበት።

አንዳንዶች ደብረ ማርቆስ የታየው በአማራነት ላይ በደንብ ስላልሰራን ነው ይላሉ። ይህ ስህተት ነው። እመኑኝ በደንብ በአማራነት ሰራን ያሉባቸው ቦታዎችም፣ የደብረ ማሮቆስ አይነት እንደውም የበለጠ ሕዝባዊ የኢትዮጵያዊነት ትእይንት ይደረግባቸውል። ከዚህ በፊት ተደረጎባቸውም ያውቃል፡፡ የፈለገ የአማራነት ፖለቲካና ፕሮፖጋንዳ ቢደረግም የአማራ ማህበረሰብ ደምና አጥንቱ ኢትዮጵያዊነት ነው። ደብረ ማርቆስ ፍንትው ባለ መልኩ ይሄንን አረጋግጣለች። የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ስነ-ልቦና ከሌላው የአማራ ክልል ስነ-ልቦና በምንም አይለየም። አማራነት ላይ በደንብ አልሰራንም በሚል የበለጠ አማራነት ላይ ከማጠንከር፣ ሕዝቡ ጋር ያለውን ይዞ፣ ከአማራነት ወደ ተሻለው፣ ከፍ ወዳለው ማደግ ይሻላል። ወደ ኢትዮጵያዊነት።

በአንጻሩ የግንቦት ሰባት ካድሬዎችም ሲቀውጡት እያየን ነው። ጎጃም የግንቦት ሰባት ነው እያሉ። አይ የካድሬ ነገር። የግንቦት ስባቱ ጦማሪ ናትናኤል መኮንን ፣ “ህዝብ እውነተኛ ዳኛ ነው ሥልህ የታገለለትን የተሰቃየለትን፣ የሞተለትን እና ለእውነት ከምር አታግሎ የሚያታግለውን ያውቃል” ሲልም የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ለግንቦት ሰባት ሰልፍ የወጣው፣ ግንቦት ሰባት ስላታገለው እንደሆነ ጽፏል። ይህ ከእዉነት የራቀ አባባል ነው።

አንደኛ – የደብረ ማርቆስ ሕዝባዊ ስብሰባን ያደራጁት ከጥቂት አመታት በፊት በዳያስፖራ፣ “የሰላማዊ ትግ አይሰራም” እያሉ፣ ግንቦት ሰባቶች ራሳቸው እንዳይደገፉ ሲዶልቱባቸው የነበሩ፣ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው። ያኔ አንድነቶች ወያኔን ብቻ ሳይሆን ግንቦት ሰባትንም ነገር ሲታገሉ የነበሩት። ስለዚህ ግንቦት ሰባቶች ያደራጁት እንዳልሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት።

የቀድሞ አንድነቶች ያንን የሚያደርጉት ለምንድን ነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ ደግሞ መልሱ ቀላል ነው። ለአገር ትቅም ሲሉ፣ ያለፈውን ረስተው፣ የቀድሞ አንድነቶች ከግንቦት ሰባት ጋር አብረው ለመስራት ከመስማማታቸው የተነሳ ነው። በነገራችን ላይ ከዚህም በፊት በአዳማና በአርባ ምንጭ የተደረጉ የግንቦት ሰባት ስብሰባዎችንም የቀድሞ አንድነቶች ነበሩ ያዘጋጁት። ያው ግንቦት ሰባት ሌላው በሰራው ክሪዴት መውሰድ የለመደ ድርጅት ስለሆነ ለቀድሞ አንድነቶች እንኳን እውቅና መስጣት አልሞከረም። ትዝ የሚላችሁ ከሆነ በጎንደር የሸፈቱ አርበኞች አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ ግንቦት ሰባት ቀድሞ በኢሳት ብቅ ይልና፣ ይሄን አደረኩ ብሎ ፕሮፖጋንዳ ይነዛ ነበር። ያው የድሮው ባህል ነው አሁን እነርሱ ጋር ያለው።

ሁለተኛ – የደብረ ማርቆስ ሕዝብ፣ ግንቦት ሰባት እንኳን ሕዝቡን ሊያደራጀና ሕዝቡን ሊያታግል ቀርቶ ሕዝቡን ላለፉት በርካታ አመታት ሲያጭበረብር የነበረ ድርጅት እንደሆነ ጠንቅቆ ያወቃል። ነገር ግን ሕዝቡ አማራጭ አላገኝም። ሕዝቡ ከአማራነት ኢትዮጵያዊነት ስለሚቀድምበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ የገንዘብ አቅም ያለው፣ ሜዲያ(ኢሳት) ያለው፣ የሚታየው፣ ለኢትዮጵያዊነት ቆሚያለሁ የሚለው ድርጅት ግንቦት ሰባት ስለሆነ፣ ለግንቦት ሰባት ብሎ ሳይሆን፣ ግንቦት ሰባት አራምደዋለሁ ስለሚለው ኢትዮጵያዊነት ሲል በነቂስ ወጥቷል። የዛሬው የደብረ ማርቆስ ሕዝባዊ ትእይንት የግንቦት ሰባት ትእይንት ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ትእይነት ነው። ጉዳዩ ያለው ግንቦት ሰባት ጋር ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ጋር ነው። ስለዚህ የግንቦት ሰባት አባላትና ደጋፊዎች ትንሽ ሰከን ብትሉ ጥሩ ነው።

አንዳንድ ወገኖች ግንቦት ሰባት ማለት ኢትዮጵያዊነት ነው ይላሉ። እኔ ይሄን አልቀበለም። ግንቦት ሰባት ኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለኝም። የግንቦት ሰባት የፖለቲካ ፕሮግራም ፣ የፖለቲካ አቋም ምን እንደሆነ አላውቅም። የዜግነት ፖለቲካ እናራመዳለን ይላሉ፣ ግን የዜግነት ፖለቲካ ጸር የሆኑትን የጎሳ አወቃቀርና ኢትዮጵያዊነትና ዜግነትን የማያንጸባርቅ ሕገ መንግስት እንዲሻሻል ሲናገሩ አይሰሙም። በኦሮሞ ክልል ኦሮሞ ስላልሆኑ ብቻ ዜጎች እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲቆጠሩ ፣ ሲፈናቀሉ፣ ልዩነት ሲደረግባቸው ያንን ሲቃወሙ፣ ለነዚህ ወገኖች ሲሞግቱ አይታዩም። ለነርሱ ዘርና ጎሳ ከተሸነሸነው መሬት ውጭ ለሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰብ የዜግነት መብት ሲከራከሩ አይሰሙም። በአዲስ አበባ ላይ ያላቸው አቋም ግልጽ አይደለም። የታከለ ኡማን አስተዳደርን የሚደገፉ ናቸው። በአጠቃላይ ግንቦት ሰባት ለሕዝብ ይፋ ያደረገው የፖለቲካ ፕሮግራም የለም። ስለዚህ ምንም ሰነድ፣ ፕሮግራምና ማኒፊስቶ ሳይኖር እንዴት ብለን ነው ግንቦት ሰባት የዜግነትና የኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካ የሚያራመድ ነው የምንለው ??

በኔ እይታ ግንቦት ስባት

– አሁን ያለው የጎሳ አወቃቀር ፈርሶ ከጎሳና ዘር ጋር ያልተገናኛ፣ ማንኛውም ዜጋ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ዘሩ፣ ሃይማኖቱ፣ ሳይጠየቅ እንደ መጤ ሳይቆጠር፣ መኖር ፣ መስራት፣ መነገድ፣ መመረጥ፣ መምረጥ ….የሚችልበት አወቃቀር እንዲኖር
– አሁን ያለው ሕግ መንግስት ዜግነት ላይ ያተኮረ መሆነ መልኩ እንዲሻሻል

የሚጠይቅ የፖለቲካ ማኒፊስቶ ይዞ ከመጣና፣ በዚህ ማኒፌስቶ ዙሪያ ለመታገል ከተዘጋጀ ድጋፌ አይለየዉም። የኔ ብቻ አይደለም፣ እንደውም እኔ ደገፍ አልደገፍኩ ብዙ የሚለወጠው ነገር የለም፣ ግን የመላው ጎጃም፣ ጎንደር፣ወሎ፣ ሸዋ፣ ቦንጋ፣ ሶዳ፣ ጂንካ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ አሰላ ….የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብን ድጋፍ ያገኛል።

ያ ካልሆነ ግን ላይ፣ ላይ ላዩን የዜግነት ፖለቲካ እያለ ፣ ውስጥ ውስጡን ግን የኦህዴድ/ኦዴፓ ደጋፊና አጋፋሪ፣ አሁን ያለው አፓርታይዳዊ የኦሮሞ ክልል እንዲቀጥል የሚፈልግና የአማራ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ብሄረተኛውን አወናብዶ ለፖለቲካ ስልጣን መንጠላጠያ ብቻ ለማድረግ የሚሰራ ድርጅት ከሆነ ግን (ላለፉት በርካታ አመታት ሲያወናብድ እንደነበረው) እመኑኝ መተፋቱ የማይቀር ነው።