የፌዴራል ገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ ሥራ ላይ ከዋለ የውጭ ኢንቨስትመንት ሊጎዳ እንደሚችል ተነገረ

የፌዴራል ገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገ የአገሪቱን የውጭ ኢንቨስትመንት ሊጎዳ እንደሚችል ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አሳሰበ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ የጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በጠራው የምክክር መድረክ የንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሒሳብ ባለሙያዎች፣ የፌዴራልና ክልል መንግሥታት ተወካዮች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የንግድ ተቋማትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ነው ማሳሰቢያው የተሰጠው፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በውይይት መድረኩ ከተገኙ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ድርጅቱን ወክለው የተገኙት አቶ ዳዊት ፍሰሐ በረቂቅ ሕጉ ላይ ቢስተካከሉ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

አንድ ድርጅት እየከሰረ መቀጠል እንደማይችልና ኪሳራው ከቀጠለ እንደሚዘጋ በረቂቅ ሕጉ ላይ መጠቀሱን ገልጸው፣ ነገር ግን እንደ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ላለ ልዩ የኢንቨስትመንት ባህሪ ላለው ተቋም የማይሠራ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡

‹‹ያለን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለ15 ዓመታት የሚል ነው፡፡ ይህ ፈቃድ በየ15 ዓመት እንደሚታደስ ሆኖ ለ30 ዓመት የሚቆይ ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ኢንቨስትመንታችን በሙሉ ለ30 ዓመታት መቆየትን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው፡፡ ኢንቨስትመንታችን ትርፍ አለ ብለን በምናስብባቸው ቦታዎች ሁሉ አይደሉም፡፡ በየቦታው ታወሮችን መገንባትን ጨምሮ ብዙ ካፒታል የሚያስወጡ ሥራዎች አሉብን፡፡ የኔትወርክ ሽፋን ለማስፋት የመገንባት ግዴታዎች አሉብን፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥ ለመሠረተ ልማት ማስፋፊያና ግንባታ ከ350 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገናል፡፡ ይህን የምናደርገው በረዥም ጊዜ ትርፍ ይመጣል በሚል ዕቅድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዳዊት አክለውም፣ ‹‹ኢንቨስት የምናደርገው ትርፍ በሚገኝባቸው ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ኪሳራ ገጠመን ብለን በትንሽ ዓመት ውስጥ ድርጅቱን ዘግተን መሄድ አንችልም፡፡ የ15 እና የ30 ዓመታት ግዴታ አለብን፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወደ ትርፍ እንመጣለን ብለን እየሠራን ባለንበት ሁኔታ፣ ‹ኪሳራ አስመዝግቧል› በሚል ሊዘጋ ይችላል መባሉ ትክክል አይደለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ለእንደ እኛ ዓይነት ኢንቨስትመንት ኪሳራ የሚጠበቅ ትርፍም ሩቅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ከግምት ውስጥ አስገብተን የመጀመሪያው ሪኮመንዴሽናችን ድፍረት የተሞላበት ቢመስልም፣ ይህ የገቢ ግብር ረቂቅ ሕግ ኪሳራ ላይ ላለ ድርጅት በፍፁም ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጫችን ደግሞ ካፒታል ኢንሴንቲቭ የሆኑ እንደ ቴሌኮም ኢንቨስትመንት ዓይነት ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ኢንቨስትመንቶች ከዚህ አማራጭ የግብር ክፍያ ሥነ ሥርዓት ውጪ እንዲደረጉ እንጠይቃለን፤›› ሲሉም በረቂቅ ሕጉ ላይ ቢሻሻሉ ያሏቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል፡፡

መንግሥት ይህንን አማራጭ የገቢ ግብር ሥርዓት ካላስተካከለ ‹‹በሀቀኝነትም ቢሆን ኪሳራ እየደረሰብን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት የምናደርገውን ጥረት ያቀጭጫል፣ እንዲሁም እንደ እኛ ዓይነት ሌሎች ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች እንዳይመጡ ሊያደርግ ይችላል፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

‹‹እኛ ትልቅ ተወዳዳሪ አለብን፡፡ ይህ ረቂቅ ሕግ በተወዳዳሪዎቻችን ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ መንግሥት ማየት አለበት፡፡ እውነተኛ ኪሳራን በሚገባ መለየት አለበት፡፡ ከእነዚህ ጫናዎች ልንጠበቅ ይገባል፤›› ያሉት አቶ ዳዊት፣ አማራጭ የገቢ ግብር ሥርዓቱ መንግሥት የጀመረውን የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽን ፕሮጀክት እንደሚጎዳውም ገልጸዋል፡፡

ሌላው በረቂቅ ሕጉ ላይ ከተሳተፉት መካከል አንዱ የሆኑት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው በበኩላቸው፣ የጥብቅና ሙያ እንደ ንግድ ሙያ ተቆጥሮ ግብር እንዲከፍል በረቂቅ ሕጉ ላይ ሊሠፍር እንደማይገባና ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የግብር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የከሰረን ተቋም በሚመለከት አነስተኛ ታክስ የማይተገበርበት አገር የለም፣ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ነው፤›› ብለዋል፡፡

አማካሪው አክለውም፣ ‹‹የረቂቅ ሕጉ ዋና መርህ መንግሥት አገልግሎት ይሰጣል፣ ከመንግሥት ለተገኘው አገልግሎት ፍትሐዊ ግብር መክፈል ግዴታ ነው፡፡ ሌላው በከፈለው ግብር እኔ ኪሳራ ላይ ነኝ እየተባለ ግብር አንከፍልም እንዳይባል ነው፡፡ አገልግሎት በነፃ ማግኘት አይቻልም፡፡ አንድ የንግድ ተቋም በትክክል ኪሳራ ውስጥ ከሆነ ኪሳራውን መንግሥትም ይጋራል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ የጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በውይይት ማጠቃለያ ምላሻቸው፣ በረቂቅ ሕጉ ላይ ከዚህ በፊት በተደረጉት ውይይቶች ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ በርካታ ማስተካከያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በረቂቅ ሕጉ ላይ ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚደረጉ የገለጹት አቶ ደሳለኝ፣ የተነሱ አስተያየቶች ተለይተው እንደሚካተቱና ሕጉ እንደሚፀድቅም ተናግረዋል፡፡