ትራምፕ አሜሪካ የኢትዮጵያውን ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በገንዘብ ደግፋለች ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ የኢትዮጵያውን ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በገንዘብ ደግፋለች ሲሉ ርግጠኝነት በሌለው መልኩ ትናንት በድጋሚ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ፣ ግድቡ ወደ ናይል ወንዝ የሚሄደውን ውሃ ይዘጋዋል በማለትም ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም፣ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ እየሠሩበት መኾኑንና ችግሩ መፍትሄ እንደሚያገኝ በደፈናው ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱ “መፍትሄ” ያሉት ምን እንደኾነ ግን አላብራሩም። መንግሥት፣ ከአንድ ወር በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ካኹን ቀደምም ይኹን ትናንት ለተናገሩት አወዛጋቢና አሳሳች አስተያየት፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም።