ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላትና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር የሕዝብ ውይይት አድርጎ ነበር
ከፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት በኋላ የተነሳው የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነቴ ይመለስልኝ ጥያቄ ፓርቲውን ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ከምርጫ ቦርድም ጋር ሲያወዛግብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ምርጫ ቦርዱ በአሸባሪነት ተፈርጆ የቆየ፣ እንዲሁም በፓርቲነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችለው ሕጋዊ ዕውቅና ተሰርዞ የነበረ አንድ ድርጅትን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚፈቅድ የሕግ አሠራር እንደሌለው ጠቅሶ ሕወሓት ከፈለገ እንደ አዲስ ድርጅት መመዝገብ እንደሚችል ምላሽ ሰጠ፡፡ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር እንደ አሸማጋይ ሆኖ ምርጫ ቦርድን ሕወሓት በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ በደብዳቤ ጠየቀ፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንዲሻሻል ሐሳብ ቀረበ፡፡ ነባሩ አዋጅ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 1332/2016 ተሻሻለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ መመርያ ቁጥር 25/2016 ወጣ፡፡ አሸባሪ ተብሎ ተሰርዞ የነበረው ሕወሓት በልዩ ሁኔታ ድጋሚ መመዝገብ ይችላል የሚል ሕጋዊ አሠራር ተበጀ፡፡
በእርግጥ ይህ ሁሉ መንገድ ተኪዶም የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት የመመለስ ጥያቄ ዕልባት አላገኘም፡፡ ነባሩ ሕጋዊ ሰውነቱን መልሶ ማግኘት እንደሚፈልግ የጠቀሰው ፓርቲው፣ በልዩ ሁኔታ ሲመዘገብ እንደ አዲስ ድርጅት የሚመዘገብበትን አሠራር ስላልተቀበለው ጉዳዩ ማወዛገቡን ቀጥሏል፡፡ በሒደት ቦርዱ ሕወሓትን የሰረዘ ሲሆን ነገር ግን የሕወሓት ዕውቅና ማስመለስ አጀንዳ በዚህም የተቋጨ አይመስልም፡፡
ይህ አጋጣሚ ግን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የምርጫ ቦርድ ለአንድ ፓርቲ ተብሎ አዋጅ፣ እንዲሁም መመርያ እስከ ማሻሻል የደረሰ ዕርምጃ የወሰደበት ሆኖ ነው የሚቀርበው፡፡ ለአንድ ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅና ብሎ ይህን ሁሉ ርቀት የተጓዘው ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በመሻሻል ላይ ባለው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተፎካከሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት ያቀረቡትን ቢስተካከሉ የሚሏቸውን ነጥቦች ተቀብሎ፣ ለአዲሱ አዋጅ ግብዓት ለማድረግ ካሳየው ፍላጎትና ካደረገው ጥረት ጋር በተነፃፃሪነት እየቀረበ ሲያስተቸው ሰንብቷል፡፡
ለሕወሓት ዕውቅና አዋጅና መመርያ በፍጥነት ወደ ማሻሻል ሲገባ የታየው የምርጫ ቦርድ ይሁን እንጂ፣ ወሳኝ በሚባል የአዋጅ ማሻሻል ሒደት ውስጥ ከተለያዩ ወገኖች የተሰጡ ግብዓቶችን ለማካተት በቂ ዕድል አልሰጠም መባሉ ጥያቄ እያጫረ ይገኛል፡፡
ረቂቅ የሕግ ማሻሻያውን ከታኅሳስ ወር መገባደጃ ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ቦርዱ ለውይይት ሲያቀርበው ቆይቷል፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጋቸው ተከታታይ የውይይት መድረኮች ላይ ረቂቁ ለምክክር ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ምርጫ ቦርዱ እነዚህን ስብሰባዎች ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ሲላቸው የቆየ ሲሆን፣ በየመድረኩ ከተሳተፉ ባለድርሻዎችም ቢሻሻሉና ቢካተቱ የሚባሉ ነጥቦችን በቃልም በጽሑፍም ሲሰበስብ ቆይቷል፡፡ ይህ ሒደት ታልፎ ለፓርላማ የቀረበው አዋጁ ወደ የሚመለከተው ወደ ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ተጨማሪ ዕይታና አስፈላጊ ማሻሻያ የማድረግ ሒደቶች ሲካሄድበት ቆይቷል፡፡
በዚህ መሠረትም ከሰሞኑ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በፓርላማው መገናኛ ብዙኃን ተሳታፊ በሆኑበት ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተካሄደ የሕዝብ የውይይት መድረክ ላይ ረቂቁን ለውይይት አቅርቦት ነበር፡፡ ይህ መድረክ አዋጁ ለመፅደቅ ወደ ፓርላማው ተመልሶ ከመላኩ ጥቂት ቀደም ብሎ የተገኘ፣ አስፈላጊ ማሻሻያ ለማድረግም ከተገኙ የመጨረሻ ዕድሎች እንደ አንዱ ሊታይ የሚችል አጋጣሚ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ከስብሰባው ተሳታፊዎች እንደተደመጠው ከሆነ ረቂቁ ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች የተሰጡ ጥቆማዎችና ግብዓቶችን አካቶ እንዲቀርብ አለመደረጉ ትልቅ ሥጋት የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደምም ይህን ሥጋት አንስተን ነበር፣ አሁንም ይህ ሳይደረግ ወይ ሳይሟላ አዋጁ ከፀደቀ አስቸጋሪ ይሆናል›› በሚል በረቂቁ ላይ የቀረቡ አስተያየቶች መበራከታቸው አዋጁ ያለፈባቸውን የአዋጅ አወጣጥና የግብዓት ማሰባሰብ ሒደቶች በተመለከተ ጥያቄ እያጫረ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን በውይይቱ የተሳተፉት አቶ ዓባይነህ ጉጆ በኢትዮጵያ 17.6 በመቶ ሕዝብ አካል ጉዳተኛ መሆኑን በመጥቀስ ይህን ያገናዘቡ አንቀጾችን አዋጁ እንዲያካትት ጠይቀዋል፡፡ የሴት አካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ማሰባሰብ የሚጠበቅባቸው የድጋፍ ፊርማ ከ2,000 ወደ 1,500 ዝቅ መደረጉ አዎንታዊ ቢሆንም፣ ነገር ግን የወንዶች አለመቀመጡ ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በምርጫ ወቅት ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አሳታፊነትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በጣት አሻራ ምርጫ ስለሚደረግ፣ ሁለት እጅ ወይም ጣት የሌላቸው አካል ጉዳተኞችን ሕጉ ያላገናዘበ መሆኑን፣ አሁን ግን በዓይን አሻራም አማራጭ ሆኖ በመቅረቡ አካታች እንደሆነ፣ ሆኖም የእጅም የዓይንም አካል ጉዳት ያለባቸው በምን ይምረጡ የሚለው ታሳቢ መደረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡
መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ከቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩላቸው፣ ለስልክም ሆነ ለሌላ ኮሙዩኒኬሽን ሩቅ የሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች ስላሉ የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ ለዕጩዎች ተጨማሪ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚታገዱበት ሁኔታ የተዘረዘረበት መንገድ ለፖለቲካ ማጥቂያነት ሊውሉ የሚችሉ ጉዳዮች ተካተውበታል፡፡ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት በመሞከር ተብሎ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ተጨባጭ ባልሆነ መንገድ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ብቻ ሳይሆን መራጩ ሕዝብም ያለበትን ችግር ታች መሬት ላይ ወርዳችሁ ብታዩ፡፡ ከአባላት መዋጮ 30 በመቶ ፓርቲዎች ማቅረብ አለባቸው መባሉ ከባድ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ወደ አምስትና አሥር በመቶ ቢወርድ ይበጃል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን ለማስቆም የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በረቂቁ ቢካተቱ ይሻላል፤›› የሚሉና ሌሎች ሐሳቦችን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ወክለው የተገኙት አቶ ጫንያለው ታፈሰወርቅ በበኩላቸው፣ በምርጫ ሒደት ቅሬታ ሲፈጠር ጉዳዩን ለአንድ ምርጫ አስፈጻሚ ቅሬታ ሰሚ አድርጎ ሙሉ ሥልጣን መስጠት ተዓማኒነትም ሆነ ተፈጻሚነትም ላይ ችግር አለው ብለዋል፡፡ የዕድሜ ጉዳይን ለምርጫ ያለውን ፋይዳ በማንሳት ምርጫ ሲመጣ መታወቂያ የሚታደልበት ሁኔታ በምን ይጣራል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይ መምህራን ወደ ተመራጭነትና ወደ አስፈጻሚነት ሲገቡ ደመወዝ ይቆረጥላቸው ብቻ ብሎ መወሰን ሳይሆን፣ ጥለውት የሚሄዱት መሥሪያ ቤትም ሊታሰብለት ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹የምርጫ ቦርድ አባላት ሥልጣን ሲለቁ ለምን ወደ ፓርቲ መቀላቀል ይከለከላሉ፡፡ የአባላት 30 በመቶ መዋጮ ይቅረብ ሲባል በአንድ ሀብታም ሊከፈል ይችላል እኮ፣ ስለዚህ አቅርብ መባሉ ምንድነው ፋይዳው? የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ቢጠይቅም፣ ነገር ግን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት አስፈላጊና አንገብጋቢ በመሆኑ በእርሱ ላይ በልዩ ሁኔታ መሥራት አስፈላጊ ነው፤›› የሚሉ ሐሳቦችን አሰምተዋል፡፡
ከቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲ ፓርቲ አቶ ባንዲራ በላቸው በበኩላቸው፣ ዜጎችን ለዕጩዎች ድጋፍ ካልሰጣችሁ ብሎ ማስገደድም እንዲሁም ለምን ትሰጣላችሁ ብሎ ማስፈራራትም በሕግ ቢከለከል የሚልና ሌሎችም ነጥቦችን አንስተዋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፓርቲ አመራር አቶ ማሙሸት አማረ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፣ ፓርቲዎች ሲቋቋሙ የሕዝብ ድጋፍ ፊርማ አግኝተው ነው ስለዚህ አባላት ዕጩ ሆነው ሲቀርቡ ድጋፍ አምጡ መባል አይገባቸውም ብለዋል፡፡ ‹‹አካሄዱ ፓርቲዎቸ በምርጫ ቦርድ የተሰጠንን ህልውና አክስሞ በአዋጅ መተካት ነው የተያዘው፡፡ ዕጩዎች 2,000 እና 3,000 ድጋፍ ካላሰባሰባቹ አትወዳደሩም ማለት በአዋጅ የሚካሄድ ጭቆና ነው፡፡ ወደ ምርጫ እንዳንሄድ የሚያሰናክል ነው፡፡ ከፓርቲ ይልቅ የግል ዕጩ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ከዚህ ቀደም ዕጩዎች ዕጩ ሲሆኑ ከመንግሥት የሚያገኙት ገቢ ይቋረጥ የሚል ሕግ ሲቀርብ፣ እንግዲያውስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የመንግሥት ሥራቸውን ለቀው ሊወዳደሩ ይገባል ስንል ተከራክረናል፡፡ በዚህም አሁን ባለው አዋጅ ከደመወዝ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ ቀይረውታል፡፡ በስድስቱም ምርጫዎች በ15 በመቶ ድምፅ ነው መንግሥት ሲመሠረት የኖረው፡፡ ወደ 85 በመቶው የባከነና ለመንግሥትነት የማይበቁ ተቃዋሚዎች የሚያገኙት ድምፅ ነው፡፡ ይህ እየታወቀ የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓትን ለመተግበር አለመሞከር ትልቅ ስብራት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፌይሰል አብዱላዚዝ በበኩላቸው፣ ስድስት ምርጫዎች ላይ ተሳትፈናል፣ ‹‹የስድስቱንም ችግር እናውቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ምርጫ ሲደርስ ሕግ ጣሹ በመጀመሪያ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ እኛ 12 ሺሕ አባላት አሉን፡፡ ለወረዳ ዕጩ ስንሆን ከእነዚህ አባላት ነው ከማን ነው የድጋፍ ፊርማ የምናሰባስበው? እኛ ገንዘብ እንዲያውም ባይሰጠንና ቢቀር ይሻለናል፡፡ 30 ዓመት ፓርቲ ነበረን፣ ብር ያገኘነው ከሁለት ዓመት ወዲህ ነው፡፡ መንግሥት የሚሰጠን ድጎማ ከሕዝብ የምናገኘውን መዋጮ ቀንሶብናል፡፡ አይበቃም ነው መባል ያለበት፡፡ በፓርቲዎች ላይ የቦርዱ ሥልጣን የት ድረስ ነው፡፡ የጋራ ምክር ቤት የመሠረትነው ለምንድነው፤›› የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
አንዳንድ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ‹መንግሥትና ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ የሚያስቀምጥና ድንበር የሚያሰምር አዋጅ ያስፈልገናል› እስከ ማለት የደረሱ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በምርጫ ወቅት ገዥውን ፓርቲ መገዳደር ፓርቲዎች የሚቸገሩት ገዥው ኃይል ማሊያ እየቀያየረ የመንግሥትን ሀብትና መዋቅር ስለሚጠቀም መሆኑን በማስታወስ፣ ይህን የሚያስቀር ሕግ እንዲበጅ ጠይቀዋል፡፡ የቦርዱ አመራሮችም ለተነሱ ሐሳቦችና ጥያቄዎች በዕለቱ ሰፊ ማባራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ማሻሻል ያስፈለገው በተግባር የታዩ ጉድለቶችን ለመሙላትና መጪውን ምርጫ የሰመረ ለማድረግ እንደሆነ ለማሳመን ጥረዋል፡፡
በፓርላማው ሞቅ ያለ የፓርቲዎች ክርክር የገጠመው አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ በጥቂት ቀናት ልዩነት ወደ መፅደቅ እንደሚላክ ነው የተገመተው፡፡ ይህ ሆኖም አዋጁን በተመለከተ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያየ አቋም እያንፀባረቁበት የሚገኝ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር ስለፓርላማው ውይይትና በአዋጁ ላይ ስላላቸው አመለካከት ሐሳብ የጠየቃቸው የሁለት ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች አቋምም የተለያየ ሲሆን ነው የታየው፡፡ በአንዱ ወገን አስፈላጊ ግብዓቶች ተካተውበት የመፅደቅ ሒደትን አዋጁ እንደተከተለ የታመነበት ሲሆን፣ በሌላኛው ወገን ግን አዋጁ የሚሰጡ ግብዓቶችን ከግምት ሳይከትና ሳያካትት ለመፅደቅ እየተዘጋጀ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሥራ አስፈጻሚ አባልና አገራዊ ምክክር ኮሚቴ ሰብሳቢ የሕግ ባለሙያው አቶ ኢዮብ መሳፍንት፣ አዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ከሞላ ጎደል አብዛኞቹ ወገኖች የሰጡትን ሐሳብና ግብዓት ለማካተት የመሞከር ሒደትን የተከተለ ነው፡፡
‹‹እኛ በሁለት መንገድ ግብዓት የምንለውን ሐሳብ ሰጥተናል፡፡ ቦርዱ ረቂቁን ሲያዘጋጅ ጀምሮ በጽሑፍ ሰንደን ሐሳብ አቅርበናል፣ በቃልም በየስብሰባው ሐሳብ ሰጥተናል፡፡ በፓርላማ አባሎቻችንም ማሻሻያ አቅርበናል፡፡ በዋናነት ወደ 25 ነጥቦችን የያዙ ማሻሻያዎችን ነበር ያቀረብነው፡፡ የእኛ ዋና ፍላጎት አዋጁ ሁለት ዓላማዎችን እንዲያሳካ ነው፡፡ አንደኛ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋትና ፉክክርን ማጠናከር የሚያስችል አዋጅ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ በሁለተኝነት አዋጁ በገዥውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር ማድረግ ምርጫ ቦርዱ የሚችልበት ዕድል እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ የአንድ ሰው የግል ሳምሶናይት የሆኑ ፓርቲዎች እንዲስተካከሉ እንፈልጋለን፡፡ አብዛኞቹ የማሻሻያ ሐሳቦቻችን ደግሞ ተካተውልናል፡፡ አንዳንዶቹ አልተካተቱልንም፡፡ ይህ ደግሞ በሕግ ማውጣት ሒደት የሚያጋጥም ነው፤›› በማለት የፓርቲያቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
አቶ ኢዮብ ሐሳባቸውን ሲቀጥሉም፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ትርጉም ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን፡፡ እኛ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ከአምስት ክልል ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሚጠበቅበት ሁሉ አንድ የክልል ፓርቲ ደግሞ ቢያንስ ከዚያው ክልል ከተወሰኑ ዞኖች ድጋፍ ማሰባሰብ አለበት የሚል ሕግ እንዲበጅ እንፈልግ ነበር፡፡ የሚሰባሰበው ድጋፍ ቁጥርም ከፍ እንዲል እንፈልግ ነበር፡፡ ይህ ሐሳብ ግን አልተካተተልንም፡፡ ምርጫ ለማድረግ አንድ ዓመት ነው የቀረን፡፡ አገራዊ ምክክሩም የቀረው ጊዜ ጥቂት ነው፡፡ በአገራዊ ምክክሩ ውስጥ በአጀንዳነት ከቀረቡ ጉዳዮች ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውም ይገኛሉ፡፡ እኛ ለምሳሌ ፕሬዚዳንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ለኢትዮጵያ ይበጃል ብለን ያቀረብነው አጀንዳ ነው፡፡ አገራዊ ምክክሩ በቀረው ጊዜ ሥራውን ለማጠናቀቅ ቃል የገባ እንደ መሆኑ መጠን፣ ምርጫ ቦርድ የሚያደርገው የሕግ ማሻሻያም ትንሽ ዘግየት ብሎ ከዚያ የሚመጡ ውጤቶችን ለማካተት ታሳቢ ቢደረግ የሚል ሐሳብ አለን፡፡ አሥር ጊዜ አዋጅ ከምናሻሽል ከአገራዊ ምክክሩ የሚመጡ ውጤቶችንም አካቶ ቢካሄድ እንላለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ስለፓርቲዎች መብዛትና አቅም ማነስ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ፣ ‹‹እኛ 80 ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ አያስፈልግም፣ ፓርቲዎች ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል ነው የምንለው፡፡ ገዘፍ ያሉ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው የሚያስፈልጉን፡፡ ጥቂት ጠንካራ ኖረው ገዥውን ፓርቲ መፎካከር ሲችሉ ነው ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ 40 እና 50 ድርጅቶች በተናጠል ሮጠው ከገዥው ፓርቲ ጋር ተፎካክሮ የምክር ቤት ወንበር በሚደረግ ሩጫ አንድም ወንበር ለማግኘት የማይችሉ ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡ ጥቂቶች በከፋቸው ቁጥር ፓርቲ የሚያቋቁሙበት ሁኔታ መቆም አለበት፡፡ መድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚያጠናክር መሆኑ በብዙ አገሮች ታይቶ የተረጋገጠው ተሞክሮ ጥቂት ጠንካራ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ሥርዓት ነው፡፡ የተጠኑ ጥናቶችም ይህን ያረጋግጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለወረዳም ወንበር የማያበቃ አቅም ያልገነቡ 50 ጥቃቅን ፖርቲዎች መኖራቸው ትርጉም የለውም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለማጠናከር መተባበርና መሰባሰብ መቻል አለባቸው፡፡ ስለማልችል በእኔ ልክ የምርጫ ቦርዱ ሕግ ይሰፋልኝ ማለት አግባብነት የለውም፤›› ሲሉ ሕጉ ይህን ዓይነቱን አካሄድ ለማስቀረት በጎ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
አቶ ኢዮብ ብዙዎች ስላልተስማሙበት የቅሬታ አቀራረብ ተጠይቀው፣ ‹‹ቅሬታ አሰማምም ቢሆን ለአንድ ሰው ተሰጠ ቢባልም ሒደቶች አሉት፡፡ አዋጁን የሚቃረኑ መመርያዎች ይወጣሉ ብለን አንገምትም፡፡ በሕግ አወጣጥ ሒደት ሁሉም ነገር በአዋጅ ሊካተት አይችልም፤›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡
‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሕዝብ ይመረጡ የሚለውን ነጥብ እኛም ስንጠይቅ ነበር፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱን አይነካም፡፡ የሕገ መንግሥቱን ክፍተት በመጠቀም አስፈጻሚው የራሱን ሰዎች ይመርጥበት ነበር፡፡ ይህ እንዲቀየር የሚያደርግ አዋጅ ነው የተበጀው፡፡ የምርጫ ሥርዓቱን በተመለከተ ግን የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ በመሆኑ፣ እሱን በአዋጁ ማካተት አይቻልም፡፡ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፓርቲዎች ተስማምተውበታል፡፡ ጉዳዩ ወደ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ሄዷል፡፡ ስለዚህ አዋጁ ከምክክር ኮሚሽኑ የሚመጡ ውጤቶችን ጠብቆ ቢያካትት የተሻለ ነው እንላለን፤›› በማለት የተናገሩት የኢዜማው አቶ ኢዮብ፣ ማሻሻያ አዋጁ ከሞላ ጎደል ግብዓቶችን ከሁሉም አቅጣጫ ለማሰባሰብ የመከረ ነው የሚል ግምገማ በኢዜማ በኩል መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አመራሯ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ደግሞ፣ ማሻሻያ አዋጁን ለማውጣት ቦርዱ እስካሁን የተከተላቸው ሒደቶች አሳታፊነት የጎደላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን ሥጋቶችና ግብዓቶች ተቀብሎ ማሻሻያ ለማድረግ በቂ ጥረት ያልተደረገበት አካሄድ ጭምር የታየበት ነው ይላሉ፡፡
ራሔል (ዶ/ር) ለሪፖርተር በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ የእሳቸው ፓርቲ በሰነድና በቃል ግብዓት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ባለፉት ስድስት ዙር ምርጫዎች የታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ወደፊት እንዳይደገሙ በሚያደርግ መንገድ ለመራመድ ታሳቢ ተደርጎ በማሻሻያ ሒደቱ ላይ ለቦርዱ በጋበዘ ቁጥር፣ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ጭምር ፓርቲዎች ግብዓት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እነዚህን ጥቆማዎች ተቀብሎ ማሻሻያ ለማድረግ በቂ ጥረት አለመደረጉ የሳስባል፤›› በማለት ነው የገለጹት፡፡
‹‹ለምሳሌ አገር አቀፍም ክልለ አቀፍም ፓርቲ ሕጉን ተከትሎ ለምርጫ ከቀረበ ዕጩ ሆኖ የሚቀርበው የፓርቲ አባል የሕዝብ ድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ ሊገደድ አይገባም፡፡ ለምርጫ የቀረበው ፓርቲው እንጂ የፓርቲው አባል በግሉ አይደለም፡፡ አባሉ ፓርቲውን ነው የሚወክለው፡፡ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለክልል ተወዳዳሪዎች ቁጥር ቀንሻለሁ ቢልም ዕጩዎች በፓርቲ እስከ ቀረቡ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሊገደዱ አይገባም፡፡ ባለፉት ስድስት ምርጫዎች ድጋፍ ለማሰባሰብ የገጠሙን ችግሮች ታሳቢ ሊደረጉ ይገባል፡፡ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ስናካሂድ አልመጣንም፡፡ ፓርቲና መንግሥት ያልተለየበት የፖለቲካ ሥርዓት ነው ያለን፡፡ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሶ ድጋፍ ለማሰባሰብ መንገድና ሌላም መሠረተ ልማት የለም፡፡ በየገጠሩ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሴቶች እስከ መደፈር ድረስ የገጠማቸው ብዙ ችግር አለ፡፡ አካል ጉዳተኞች በዚህ ሁኔታ ድጋፍ ማሰባሰብ እንዴት ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የዕጩዎች ምዝገባ ሳያልቅ ግጭት ሲፈጠር ታዝበናል፡፡ የተሰበሰቡ የድጋፍ ወረቀቶች የተቀሙበት አጋጣሚ በግል አጋጥሞኛል፡፡ እኔ ድጋፍ ላሰባስብ በተገኘሁበት የተሰበሰቡ የአንድ መንደር ነዋሪዎች ከአካባቢው የብልፅግና ሹም ከባድ ማስፈራሪያ እኔ ባለሁበት አጋጥሟቸዋል፡፡ አንዲት አሮጊት እንዲያውም ከፈለግህ አይኔን አጥፋው ሲሉ ነበር በድፍረት ለሰውዬው የመለሱለት፡፡ ይህ ሁሉ ገና ዋናው ፉክክርና ምርጫው ሳይደረግ የገጠመን ችግር ነው፡፡ ይህ ሁሉ አሁን ለሚዘጋጀው ማሻሻያ አዋጅ ግብዓትነቱ አልታየም፡፡ ለግል ተወዳዳሪም ቢሆን ዕጩ ሆኖ ሲቀርብ የድጋፍ ፊርማ ካላመጣህ ማለቱ ምኑ ላይ ነው ዴሞክራሲያዊ ፉክክርን የሚያሳድገው? ጉዳዩ በሎጂክም በሕግም የማያስኬድ ነው፣ ሕዝብን አማራጭ ያሳጣል፡፡ ድጋፍ የሚሰበሰበው ከዜጎች ነው፡፡ ዜጎች ደግሞ የማንኛውም ፓርቲ ደጋፊና አባል የመሆን መብት አላቸው፡፡ ከምርጫ በፊት ድጋፍ ስጡኝ ማለት እንዴት ያስኬዳል፡፡ ሌላው ከፍተኛ ቅሬታ ያስነሳው የተቃዋሚዎች የአባላት መዋጮን 30 በመቶ ማሳወቅ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት በበጀትነት የሚጠቀመው ገንዘብ እኮ ከተቃዋሚዎች ጭምር ከሚሰበሰብ ግብርና ታክስ የሚገኝ ነው፡፡ የአገሪቱ ሀብት መንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሀብት ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ሀብት የተቃዋሚዎችና የሁሉም ሀብት ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ነው በቦርዱ ፓርቲዎች ገንዘብ እንዲሰጣቸው የተደረገው፡፡ ገና ለገና ገንዘብ ሰጠን ቁጥጥር ማድረግ አለብን ተብሎ የፓርቲዎችን የውስጥ ደንብና አሠራር የሚጥስ አካሄድ መከተል ተገቢነት የለውም፡፡ አንድ ፓርቲ ሲጠየቅ ለይስሙላ ገንዘቡን አስገብቶ አካውንት አሳይቶ ብቻ በኋላ በፈለገው መንገድ ከሄደ በምን ቁጥጥር ሊደረግበት ነው፡፡ መዋጮ ከተነሳ ደግሞ ገዥው ፓርቲ እኮ ከመላው የመንግሥት ሠራተኞች የተቃዋሚዎች አባልና ደጋፊ ከሆኑ ጭምር አንቆ እየተቀበለ ነው ሀብት የሚያከማቸው፡፡ የመሬት ግብር ደረሰኞች ላይ ጭምር ለብልፅግና ተብሎ መዋጮ እንደሚደረግ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ ነገ ሌላው ወደ መንግሥት ሲመጣ ይህን መሰል ነገር እንዳይደገም የሚያደርግ ተሻጋሪና በመሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ያገናዘበ አዋጅ ነው የሚያስፈልገን፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎች 30 በመቶ ሴት ዕጩዎችን ማቅረብ አለባቸው ተብሎ የተቀመጠውም ተጨባጩን ሀቅ ያገናዘበ አይደለም፡፡ እኔም ሴት ነኝ፣ ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዲቀላቀሉ መበረታታት አለባቸው ነው የምለው፡፡ ሴቶች ያውም በእኛ አገር ያውም ወደ ፖለቲካ ለመምጣት ግን ብዙ መስዋዕትነት እንደሚጠይቃቸው ይታወቃል፡፡ ወደ 30 በመቶ ሴት ዕጩዎችን ለማቅረብ የማይቸገሩ ፓርቲዎች እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ ሆኖም የምንኖርበትን ሁኔታ እናውቀዋለንና ፓርቲዎች 30 በመቶ ሴት ዕጩ ካላቀረቡ ተብሎ በአዋጅ መቀመጡ ተገቢነት አለው ብዬ አላምንም፤›› በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ራሔል (ዶ/ር) በምርጫ ወቅት የሚቀርቡ ቅሬታዎች አሰማምና አፈታትን በተመለከተ የቀረበው ጥቆማም ተቀባይነት አለማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ ከግብዓት ማሰባሰቢያ ስብሰባዎች ጀምሮ በአዋጁ ላይ ፓርቲዎች ያሏቸውን ቅሬታዎችና ቢካተቱ የሚሏቸውን በሰፊው ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ነገር ግን እስካሁንም እነዚህን ግብዓቶች ለማካተት የተደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ አምስት ጉዳዮች ግብዓት ተቀብለን አሻሻልን ብለው ቢያቀርቡም ነገር ግን ውይይት ሳያስፈልግ ሁሉ በሒደት ሊታረሙ ይገባቸው የነበሩ ነጥቦችም ተዘለዋል፤›› የሚሉት ራሔል (ዶ/ር)፣ እስካሁን የተደረጉ የግብዓት ማሰባሰብ ስብሰባዎች ከሞላ ጎደል የሚፈለገው ውጤት ያልተገኘባቸው መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ባለ84 ገጹ አዲሱ የምርጫ ቦርድ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ባለፉስት ስድስት ዓመታት ያገለገለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለመተካት የቀረበ ነው፡፡ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ዘጠኝ ክፍሎች፣ 18 ምዕራፎች፣ እንዲሁም አምስት ንዑስ ክፍሎችና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ይዞ የቀረበ ነው፡፡ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ውስጥ የነበሩ አንቀጾችን ከማሻሻልና ከመለወጥ በዘለለ አዳዲስ ጉዳዮችንም አክሎ የቀረበ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲሱ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በነባሩ አዋጅ የነበሩ አራት የምርጫ ዓይነቶችን፣ ማለትም የጠቅላላ ምርጫ፣ ከአካባቢ ምርጫ፣ ከማሟያ ምርጫና የድጋሚ ምርጫ ዓይነቶች ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫን እንደ አምስተኛው የምርጫ ዓይነት አክሎ አቅርቧል፡፡
ለአንድ የምርጫ ዘመን ብቻ ሥራ ላይ የዋለውን ነባሩን አዋጅ በብዙ መንገዶች የለወጠ ስለመሆኑ የተነገረለት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 10 ላይ፣ ‹‹እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ቁጥር ከ1,000 መብለጥ የለበትም፤›› በማለት እስካሁን ሲሠራበት የቆየውን 1,500 ቁጥር ቀንሶታል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 61 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን የተመለከተ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ በንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይም ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ፣ የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲወከሉ ያደርጋሉ›› ተብሎ ተደንግጓል፡፡ የኢዜማው አቶ ኢዮብም ሆነ አንዳንዶች አዲሱ የምርጫ ቦርድ ማሻሻያ አዋጅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሕዝብ የቀጥታ ድምፅ እንዲመረጡ ይደረጋል መባሉ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጣረስ ቢከራከሩም፣ ከዚህ ድንጋጌ ጋር እንዴት ታርቆ እንደሚሄድ ግን የተብራራ ነገር ማግኘት አልተቻለም፡፡