” እሳተ ገሞራው እንደፈነዳ መረጃው ደርሶናል፣ ከዚህ በፊት ያልነበረ በጣም ከፍተኛ አቧራ እየወጣ ነው ” – ሰመራ ዩኒቨርሲቲ
በአፋር ክልል የኤርታሌ እሳተ ገሞራ እየፈነዳ መሆኑን ሰመራ ዩኒቨርሲቲና አንድ የዘርፉ ባለሙያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የጂዖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ኖራ ያኒሚኦ በሰጡን ገለጻ፣ እሳተ ገሞራው መፈንዳቱን ከአካባቢው ማህበረሰብ ማረጋገጣቸውን ገልጸው፣ ለነዋሪዎቹ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈዋል።
” እሳተ ገሞራው እንደፈነዳ መረጃው ደርሶናል፣ ከዚህ በፊት ያልነበረ በጣም ከፍተኛ አቧራ እየወጣ ነው ” ያሉት ተመራማሪው፣ ” በአካባቢው በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ቢያንስ እዛ አካባቢ ያለውን ህዝብ ማራቅ የሚቻልበት መንገድ ቢፈጠር ጥሩ ነው ” ሲሉ አስገንዝበዋል።
” ኤርታሌ በቀን በጣም ብዙ ሰው የሚጎበኘው ቦታ ስለሆነ ወደዚያ የሚሄዱ ጎብኝዎች ጥንቃቄ ያድርጉ፣ ምክንያቱም የሚፈጠረው ነገር አይታወቅም ” ሲሉም ተናግረዋል።
” ከዚህ በፊት ኤርታሌ ላይ እንደዚህ አይነት ነገር የተለመደ አልነበረም፣ እሳት ገሞራ ከመፍሰስ ውጭ፣ አሁን ግን ብናኞቹ ወደሰማይ እየወጡ ስለሆነ ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል ” ያሉት አቶ ኖራ፣ ክስተቱ እስከሚረጋጋ ድረስ ወደ አካባቢው ቀርበው ፎቶ የሚያነሱ ሰዎች እየተስተዋሉ በመሆኑ ከዚህ ተግባር እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
አክለው፣ ” አንድ ልጅ በጣም ተጠባብሶ ፎቶ እያነሳ ነበር ” ሲሉ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቅናቸው አንድ የዘርፉ ባለሙያ በበኩላቸው፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታው እንደተከሰተ ገልጸው፣ ጉዳዩን ይበልጥ ለማጣራት በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ፣ መረጃውን አጣርተውም ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚሰጡን ነግረውናል።
ግን እሳተ ገሞራው ተከስቷል መባሉ ትክክል ነው ? ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም “እውነት ነው። እየፈነዳ እንደሆነ ሰምቻለሁ፣ ፎቶግራፎችም ደርሰውኛል ” ብለዋል።
” ዛሬ ምሳ ሰዓት አካባቢ እንደተከሰተ ነግረውኛል፤ ከአፋር ክልልም ደውየ አጣርቻለሁ ” ብለው፣ ” የሳተላይት መረጃዎችን እያጠናከርን ነው ” ሲሉም ተናግረል።
በአካባቢው ላለፉት በርካታ ዓመታት ተደጋጋሚ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ያስተናገደ ሲሆን፣ በተለይም ከ2017 ዓ/ም ጀምሮ ከፍተኛ ፍንዳታዎችን እንደታዩ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ በስፋት እንደተከሰተ ይታወሳል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ