አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ በአዲስ መዋቅር ስር ሆኖ እንደሚቀጥል አስታወቀች
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) ቢዘጋም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈጸሙ “የሁለትዮሽ የእርዳታ ስምምነቶች” በሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስር በተዘረጋው አዲስ መዋር እንደሚቀጥሉ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ። ኤምባሲው ዋነኛ ናቸው ያላቸው የሰብአዊ እርዳታ፣ ዓለም አቀፍ ጤና እና የምግብ ዋስትና መርሃ ግብሮች በአዲሱ መዋቅር እንደሚቀጥሉ ዛሬው ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
አሜሪካ በእነዚህ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ እንደሚቀጥል ኤምባሲው ማረጋገጫ የሰጠው፤ የሀገሪቱ ተራድኦ ደርጅት የሆነው USAID ባለፈው ምንት በይፋ መዘጋቱን ተከትሎ ነው። ላለፉት 64 ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሰብአዊ እና የልማት እርዳታ ሲያቀርብ የቆየው ይህ ተቋም የተዘጋው፤ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ድርጅቱን ቀስ በቀስ ሲያዳክመው ከቆየ በኋላ ነው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ ድርጅቱ የነበሩትን ኃላፊነቶች ካለፈው ሰኞ ሰኔ 24፤ 2017 ጀምሮ በይፋ ተረክቧል። ሽግግሩ “ድግግሞሽን ለመቀነስ”፣ “ተጠያቂነትን ለማጠናከር” እና የእርዳታ መርሃ ግብሮችን ከዩናይትድ ስቴትስ “የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የብሔራዊ ደህንነት ዓላማዎች ጋር ለማጣጣም የሚያስችል” ሆኖ እንደተቀረጸ የአሜሪካ ኤምባሲ በዛሬው መግለጫ ጠቁሟል።