የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ላይ ይደረጋል የተባለ ማሻሻያ ለምን ሥጋት ፈጠረ?

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ላይ ሊደረጉ የታቀዱ ማሻሻያዎችን የመረመሩ ባለሙያዎች ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሳለ ዘርፉን ቀፍድደው የያዙ ገደቦች እና አሠራሮች ተመልሰው ተግባራዊ ሊሆኑ ነው የሚል ብርቱ ሥጋት አላቸው። ሦስት እንግዶች የተሳተፉበት ውይይት ማሻሻያዎቹን እና ተጽዕኖዎቻቸውን ይፈትሻል።

ኢትዮጵያ መንግሥት “አፋኝ” ይባል የነበረውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በየካቲት 2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ሲተካ አድናቆት እና ቅቡልነት አግኝቶ ነበር።

የዐቢይ መንግሥት በኢትዮጵያውያን እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሞገስ የተቸረው ፖለቲካ ፓርቲዎችንመገናኛ ብዙኃን እና የሲቪል ድርጅቶችን የተመለከቱትን ጨምሮ የኢሕአዴግ አስተዳደር ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግባቸውን ሕግጋትን በማሻሻሉ ነበር።

መንግሥት ለስድስት ዓመታት ገደማ ሥራ ላይ የቆየውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ለማሻሻል ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል። ሕጉ የሚሻሻለው ነባሩ አዋጅ “ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል” እንደሆነ የፍትኅ ሚኒስቴር ለውይይት ያቀረበው እና ዶይቼ ቬለ የተመለከተው ሠነድ መግቢያ ላይ ሠፍሯል።

ኦፊሴላዊ ባልሆነው ሠነድ “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ የህዝብ እና የአገርን ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ” የሚለው ከማሻሻያው ዓላማች መካከል ተካትቶ ቀርቧል። ሠነዱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ቦርድ አደረጃጀት፣ የድርጅቶች ምዝገባ፣ የሥራ ነጻነት፣ የሐብት አሰባሰብ እና አስተዳደር በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ለውጦች እንዲደረጉ ምክረ-ሐሳቦች የቀረቡበት ነው።

ሠነዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ቦርድ አባላት ቁጥር ከአስራ አንድ ወደ ሰባት ዝቅ እንዲል ምክረ-ሐሳብ ቀርቧል። ከሰባቱ የቦርድ አባላት አራቱ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች ይሆናሉ። ሁለቱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሚሰየሙ ተወካዮች ሲሆኑ በሲቪል ማህበራት ዘርፍ እውቀትና ልምድ ያለው ባለሙያ በፍትኅ ሚኒስትሩ በቦርድ አባልነት እንዲካተት ሐሳብ ቀርቧል።

ማሻሻያው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ለአገር ደህንነት ስጋት መሆኑ” ያመነበትን ድርጅት የሚያቀርበውን የምዝገባ ጥያቄ ያለመቀበል ሥልጣን ይሰጣል። የፍትሕ ሚኒስቴር እና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን “ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከተወከሉ ባለድርሻ አካላት ጋር” የተወያዩበት ሠነድ ምርጫን የተመለከተ ጉዳይም ተካቶበታል።

ሀገር በቀል የሲቪል ተቋማት ከውጪ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያውያን ካልሆኑ ሰዎች “የፋይናንስ ወይም የቴክኒካል ድጋፎችን” ከተቀበሉ “የፖለቲካ አድቮኬሲ፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ወይም ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ መሠማራት አይችሉም” የሚል ምክረ-ሐሳብ በማሻሻያው ተካቶበታል።

የቀረቡት ምክረ-ሐሳቦች ለውጥ ሳይደረግባቸው የአዋጅ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ እና ከጸደቀ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚገጥማቸው ሠነዱን የመረመሩ ባለሙያዎች ሥጋት አላቸው። ሦስት እንግዶች የተሳተፉበት ውይይት በሠነዱ የቀረቡ ምክረ-ሐሳቦችን እና የሚያስከትሉትን ለውጥ ይፈትሻል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ ሐይማኖት አሸናፊ፣ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሰብአዊ መብቶች መርሐ-ግብር ተባባሪ ዳይሬክተር ዶክተር አባድር ኢብራሒም እና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ተማሪ እና ተመራማሪ ሕሊና ብርሀኑ በውይይቱ ተሳትፈዋል።

በዚህ ውይይት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከፍትኅ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተወካይ ለመጋበዝ የተደረገ ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ https://www.dw.com/am/