መንግሥት “ለሽብር ተልዕኮ የተመለመሉ” ያላቸውን 82 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የመንግሥት የዜና ምንጮች ማምሻውን ዘግበዋል። በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ የሽብር ቡድኑ በሶማሊያዋ ፑንትላንድ ራስ ገዝ አሰልጥኖ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሠማራቸውና ለቡድኑ “ሁለንተናዊ ድጋፍ” ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች እንደኾኑ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙባቸው አካባቢዎች መካከል፣ አዲስ አበባ፣ የኦሮሚያው ሸገር ከተማ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ጅማ እንዲኹም በአማራ ክልል ከሚሴ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥልጤ ዞንና ሃላባ ቁሊቶ ከተማ፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማና ሐረሪ ክልል እንደሚገኙበት ተገልጧል፡፡ ቡድኑ ለምልመላና ለጥፋት ተልዕኮው የሃይማኖት ተቋማትን በሽፋንነት ሲጠቀም እንደነበርና ሕዝብን “ለአመጽ” እና “ሁከት” የሚያነሳሱ አስተምህሮዎችን ለማስፋፋት ሙከራ ሲያደርግ ነበር ተብሏል።