
የፎቶው ባለመብት, EHRC
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር እና የዘርፍ ኮሚሽነር የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ እና የሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት ርግበ ገ/ሐዋርያ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ምንጮችች ገልፀዋል።
ኮሚሽነሮቹ ለምክር ቤቱ የሦስት ወር ማስጠንቀቂያ ጊዜ መስጠታቸውን ምንጮች የተናገሩ ሲሆን፤ ስለ ሥራ መልቀቂያው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በዋና ኮሚሽነሩ በኩል እንደተነገረ ቢቢሲ ከምንጮቹ ተረድቷል።
የከፍተኛ ኮሚሽነሮቹ የሥራ መልቀቅ ከአዲሱ ዋና ኮሚሽነር “የአመራር ስልት” ጋር በተያያዘ “ተገፍተው” እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኮሚሽኑ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“አሳታፊነትን” ይከተል የተነበረው የተቋሙ አሠራር ባለፉት ወራት ለሥራ ኃላፊዎች እና ለሠራተኞቹ ውሳኔዎቹን “አለማሳወቅ፣ አለማሳተፍ እና መመካከርን” ወደ ጎን ማለቱ ለኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች መልቀቅ እንደ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት ኮሚሽኑ ገለልተኛነቱን እና ነፃነቱን ለማስጠበቅ ባደረጋቸው መዋቅራዊ እና ተጨባጭ ለውጦች ሲወደስ የነበረ ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታ “የፓሪስ መርሆዎች” በተሰኘው መለኪያ በተአማኒነቱ ከፍተኛውን ደረጃ ‘ኤ’ ተሰጥቶታል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ሰኔ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ “የተዛባ” ሪፖርት ያወጣል የሚል ይፋዊ ወቀሳ የገጠመው ሲሆን፤ “እኛ ነፃ ሆነው ይሥሩ ስንል የጠለፏቸው . . .” በማለት በስም ያልጠቀሷቸው አካላት ጣልቃ ገብነት አለ ብለዋል።
ኮሚሽኑ አዲስ ዋና ኮሚሽነር ከተሾመለት በኋላ አራት የሚሆኑ የክትትል መግለጫዎችን ያወጣ ሲሆን፤ ስለታገዱት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ውጥረት እና ወደ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች አያያዝ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ማቆም አድማ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው።
ኮሚሽኑ ከዋና ኮሚሽነሩ ሹመት ከስድስት ቀናት አስቀድሞ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሳስ 2017 ዓ.ም. ድረስ የሩብ ዓመት ሪፖርቱን ጥር አጋማሽ ላይ አውጥቷል።
መጋቢት አሊያም ሚያዚያ ወር የሩብ ዓመት ሪፖርትን ጨምሮ ግጭት ባለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች እና በሌሎችም ቦታዎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን መርምሮ ሪፖርቱን ማውጣት አለበት።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ እና ኮሚሽነር ርግበ ገ/ሐዋርያ ሰኔ 18/2013 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ጉባኤ የተሾሙ ሲሆን፣ ተቋሙ ባካሄደው ለውጥ ስማቸው ይነሳል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ የኢሰመኮ የማቋቋሚያ አዋጅ እስኪሻሻል ድረስ ለአንድ ዓመት ያህል ከፍተኛ የስትራቴጂክ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የኮሚሽኑን “ማሻሻያ እና አደረጃጀት” ሲመሩ ከቆዩ በኋላ ነበር በዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ታጭተው ከአራት ዓመታት በፊት የተሾሙት።
በበርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሠሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ፤ በእስያ፣ በምዕራብ እና በማዕከላዊ አፍሪካ በለተያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸውን የሥራ ማኅደራቸው ያሳያል።
ኮሚሽነር ርግበም በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሰው ኃይል እና የአካል ጉዳተኞች አማካሪ እንዲሁም በግላቸው የአካታችነት አማካሪ ድርጅት ከፍተው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ነው ወደ ኢሰመኮ ኃላፊነት የመጡት።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 22/2017 ዓ.ም. የሥራ ዘመናቸውን ባጠናቀቁት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ምትክ አቶ ብርሃኑ አዴሎን ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟል።
አዲሱ ኮሚሽነር እስኪሾሙ ድረስ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ሆነው ተቋሙን ለሰባት ወራት ያህል መርተዋል።
የአዲሱ ዋና ኮሚሽነር ሹመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “የአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ጠንካራ አመራር እና ውጤታማ የሰብዓዊ መብቶች ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን” ገልጸው ነበር።
ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በተሾሙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ የተቋሙን ነፃነት እና ገለልተኝነት አስጠብቀው ኮሚሽኑን አንድ እርምጃ ለማራመድ እንደሚሰሩ ተናግረው ነበር።
ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኃላፊነት ለመሰናበት የሥራ መልቀቂያ ያስገቡት ኮሚሽነሮችን አስተያየት ለማግኘት ቢሞክርም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የእነዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሥራ መልቀቅ ለኮሚሽኑ እና ለአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ አዎንታዊ ሥራዎች “መቀልበስ” እንደምታ እንደሚኖረው ምንጮች ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ አሁናዊ አካሄድ ለሽግግር ጊዜ የሰጠ አለመሆኑ በማንሳት የተቋሙ “ቀጣይነት” ላይ ስጋት መደቀኑን አልሸሸጉም።
በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ የኮሚሽነሮች የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ሲሆን፣ አንድ ተሿሚ ከኃላፊነቱ ከሚነሳባቸው ስድስት ምክንያቶች ውስጥ በፈቃደንኝት ሥራ መልቀቅ አንዱ ነው።
በኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ተሻሚዎች የሥራ መልቀቂያ ሲያቀርቡ “ልዩ አጣሪ ጉባኤ” ተቋቁሞ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ “ትክክለኛነቱ ከታመነበት” እና በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ይሁንታ ሲያገኝ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ይደነግጋል።