ዳንጎቴ ግሩፕ በሸገር ከተማ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ፈቃድ ማግኘቱ ተገለጸ

ዳንጎቴ ግሩፕ በኦሮሚያ ክልል ሙገር አቅራቢያ ከሚገኘው የሲሚንቶ ፋብሪካ በተጨማሪ፣ ሁለተኛውን የሲሚንቶ ፋብሪካ በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ ለመገንባት ፈቃድ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡

ኩባንያው ከአንድ ወር በፊት የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ከከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፈቃድ ማግኘቱን፣ ፈቃዱን ያገኘውም የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት መሆኑን ሪፖርተር ከሸገር ከተማ አስተዳደር ምንጮቹ አረጋግጧል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ገና በማደግ ላይ ያለ በመሆኑና ለኢንቨስትመንት የሚመቹ በርካታ ቦታዎችን ለመጠቀም በተያዘው ዕቅድ መሠረት፣ የዳንጎቴ ግሩፕ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ታውቋል፡፡ መሬቱን ለመቀበልም መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች እየተሠራባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

ፈቃዱ በተሰጠበት ወቅት ከአሥር በላይ ለሚሆኑ ድርጅቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑን፣ በአሁኑ ጊዜ የሁሉም ፕሮጀክቶች ሳይት ፕላን ተነስቶ እየተሠራ መሆኑን የሸገር ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ዓብይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ደብዳቤ ወስደዋል፤›› ያሉት አቶ ነብዩ፣ ቀጣይ የሊዝ ውልና ክፍያ በመፈጸም የመሬት ርክብብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ዳንጎቴ በምን ያህል ካፒታል ለመገንባት እንዳቀደ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ የዳንጎቴ ግሩፕ የሥራ ኃላፊ ዝርዝር መረጃውን ለመስጠት ፈቃኛ ባይሆኑም፣ በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ፈቃድ ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ፋብሪካው የሚገነባበትን መሬት ምልከታ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዳንጎቴ ግሩፕ እ.ኤ.አ በ2015 ሥራ የመጀመርያውን የሲሚንቶ ፋብሪካው በ500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግንባትውን አጠናቆ ሥራ ከጀመረ በኋላ፣ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ፋብሪካው በሚገኝበት ኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሠራተኞች ዕገታና ግድያ በተደጋጋሚ አጋጥሞት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ናጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ በኦሮሚያ ክልል ካላቸው የሲሚንቶ ፋብሪካ በተጨማሪ፣ በሌሎች የኢንቨስትመን መስኮች ለመሰማራት መወሰናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም በማዳበሪያና በስኳር ምርቶች ባላቸው ልምድ በኢትዮጵያ ለመሥራት ማቀዳቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር የመጀመሪያ ዙር የጋዝ ምርት ለገበያ እንደምታቀርብ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ አንደሚጀምርና ከ40 ወራት በኋላ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር