በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ስለፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጠቡ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክተው ስላደረጉት ንግግርም ሆነ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠርተው ስለነበራቸው ውይይት ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጠቡ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታው ሀደራ አበራ (አምባሳደር)፣ ከአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ጋር ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት ማድረጋቸውን ገልጾ ነበር፡፡

ውይይቱን በተመለከተም ሆነ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ንግግር አስመልክቶ ሪፖርተር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ያልተሳካ ሲሆን፣ በዋትስአፕ ጥያቄ የቀረበላቸው አምባሳደር ማሲንጋ ከሚኒስትር ደኤታው ጋር ስለነበራቸው ቆይታም ሆነ ስለትራምፕ ንግግር ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመግለጽ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰኔ ወር ውስጥ ‹‹ትሩዝ›› በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ በከፍተኛ መጠን ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ውኃ ለሚገድበው ለግዙፉ የህዳሴ ግድብ አገራቸው ‹‹በሞኝነት›› የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን አስታውቀው፣ ነገር ግን በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ሰላም እንዲወርድ ጥረት ማድረጋቸውን በመጥቀስ፣ የሰላም ኖቤል ሽልማት ይገባቸው እንደነበር መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ፒት ረትና ከተለያዩ ሹማምንቶቻቸው ጋር በዋይት ሐውስ ሲወያዩ፣ በዓለም ግዙፍ ከሆኑ ግድቦች አንዱ የሆነውና ‹‹ከግብፅ ወጣ ብሎ የሚገኘው›› ያሉትን የታላቁ የህዳሴ ግድብ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ትልቅ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህኛውም ንግግራቸው አገራቸው አሜሪካ ግድቡን ፋይናንስ ማድረጓን ጠቅሰው፣ የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ችግሩ ለምን እንዳልተፈታ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ትራምፕ የዓባይ ውኃ ለግብፅ ህልውና መሠረት መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ግድቡ የውኃ ፍሰቱን እንደሚቀንስባት ነው የተናገሩት፡፡ ይህንን ንግግራቸውን የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በቁጣ ለግብፅ ማዳላታቸውን በመጥቀስ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ግብፅ ‹‹ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች›› ካሉት ጋር በማነፃፀር ወቀሳ እያቀረቡባቸው ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካን አምባሳደር ለምን እንደጠራና እንዳነጋገረ በይፋ ባይገለጽም፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተደጋጋሚ ስለህዳሴ ግድብ ጉዳይ ያደረጉት ንግግር ለመጠራታቸው ምክንያት መሆኑን ከምንጮች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ሪፖርተር የዶናልድ ትራምፕን የሰኔ ወር ንግግር አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው (አምባሳደር)፣ ግድቡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ታላቅ አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን በመግለጽ፣ የትብብር እንጂ የግጭት መንስዔ እንዲሆን እንደማይፈለግ ተናግረው ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብ ወጪ ከማንም ኢትዮጵያዊ የተደበቀ አለመሆኑን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከታች ከዝቅተኛው ገቢ ከላው ጀምሮ ካለው ቆንጥሮ በማዋጣት በከፍተኛ ርብርብ የተገነባ መሆኑንም አክለው ነበር፡፡ ‹‹ይህም ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፣ ማን ገነባው የሚለውን ማንሳትም ተገቢ አይመስለኝም፤›› ነበር ያሉት፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በፕሬዚዳንታዊ ጽሕፈት ቤታቸው በወጣው መግለጫ፣ የዶናልድ ትራምፕን ንግግር በአዎንታዊነት መቀበላቸውን ማስታወቃቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ አልሲሲ በፕሬዚዳንት ትራምፕ አመራር አሜሪካ ለውዝግቡ መፍትሔ ለመስጠት ያሳያችውን ቁርጠኝነት አደንቃለሁ ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹የዓባይ ውኃ የግብፃውያን የሕይወት ምንጭ፤›› ነው በማለት ዕውቅና መስጠታቸውን በማድነቅ፣ እንዲህ ዓይነቱ ዕውቅና የግብፅን ታሪካዊ የውኃ መጠቀም መብት የሚያረጋግጥና የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ማረጋገጫ ለመስጠት ይረዳል ማለታቸው ተገልጿል፡፡

በመጋቢት 2003 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ14 ዓመታት በኋላ በመጪው መስከረም ወር የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ እንደሚከናወን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡