የቀይ ባሕር አካባቢ መንግሥታት ዉስብስብ ግጭትና ዉጥረት

DW Amharic  :  ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አልሲሲ ሐገራቸዉ ድንበር ጋዛ ዉስጥ የሚደርሰዉ እልቂት፣የቀይ ባሕር ጥቃት፣የየመን መደብደብ፣ የሱዳንና የሊቢያ ትርምስ ያሳስባቸዉ ይሆናል።ሰሞኑን በጣም ያሳሰባቸዉ ግን ከሶማሊያ ፕሬዝደት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ጋር አምና ነሐሴ የተፈራረሙት ሥልታዊ ወዳጅነት ነዉ  …..

የየመን ሁቲዎች ከእስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስና ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር የገጠሙት መጠቃቃት ለቀይ ባሕር አካባቢ ሐገራት «የሩቅ» ጠብ ተብሎ የሚታለፍ ዓይደለም።የአዲስ አበባና የአሥመራ ገዢዎች  የቃላት ጦርነትና የዲፕሎማሲ ሽኩቻ እየናረ ነዉ።በህግ የታገደዉ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና የትግራይ ኃይሎች የሚባለዉ ጦር ለሁለት ተገመሰዉ አንደኛዉ አንጃ ከአሥመራ፣ሌለኛዉ ከአዲስ አበባ ገዢዎች ጋር «ፍቅር እንደገናን እያቀነቀኑ ነዉ።» ይባላል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በትግራይ ክልል ጦርነት «እንዲጫር አንፈልግም» ባሉ በሳምንቱ የትግራይ ቀሳዉስት «ለሽምግልና» አዲስ አበባ ገብተዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን ባሳወቁ በአራተኛዉ ቀን ደግሞ የግብፅና የሶማሊያዉ ገዢዎች«ሥልታዊ» ያሉትን ዉይይት አድርገዋል።ከዚያስ?

የተቃራኒዎች አንድ አቋም አብነት፣ የቀይ ባሕር ሥጋት

እሥራኤል በጋዛ ፍልስጤማዉያን ላይ የምትፈፅመዉ ግድያ፣እመቃና ማስራብን ፓኪስታን በተደጋጋሚ አዉግዛለች።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ በፍልስጤሞች ላይ በተፈፀመዉ የጦር ወንጀል ተጠርጥረዉ የዓለም የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC) እንዲታሰሩ አዝዟል።

በፍልስጤሞች ላይ የሚደርሰዉን ግፍ የምታወግዘዉ ፓኪስታንም፣ በፍፍልስጤሞች ላይ በተፈጸመ የጦር ወንጀል የሚጠረጠሩት ኔታንያሁም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ታላቅ ሽልማት ኖቤል እንዲሸለሙ እኩል አጭተዋቸዋል።የተቃርኖ «አንድነት» ይባል ይሆን?

ዋሽግተን ዲሲ።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ያጩበትን ደብዳቤ ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ሲያስረክቡ።
ዋሽግተን ዲሲ።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ያጩበትን ደብዳቤ ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ሲያስረክቡ።ምስል፦ Kevin Lamarque/REUTERS

ተባለም አልተባለ ኔታንያሁ ትራምፕን ለኖቤል ሽልማት ያጩበትን ደብዳቤ ለአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ከማስረከባቸዉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የእስራኤል አየር ኃይል የየመንን አዉሮፕላን ማረፊያና ወደቦችን ይፈረካክስ ነበር።ሐምሌ 7፣ 2025 (ዘመኑ በሙሉ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) የየመን ሁቲዎች አፀፋ ብዙም አልዘገየ።የሁቲ ታጣቂዎች «ወደ እስራኤል ይቀዝፋሉ» ያሏቸዉን ሁለት መርከቦች በተከታታይ አሰመጡ።

የዉሮጳ ሕብረት ባሕር ኃይልና ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች እንዳስታወቁት ከሁለቱ መርከቦች ቢያንስ አንዱ ወደ ግብፁ ሲዊስ ቦይ የሚቀዝፍ ነበር።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልል የምክር ቤት እንደራሴና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት የእስራኤል ጦር ድብደባም ሆነ የየመን ሁቲዎች አፀፋ ለጊዜዉ የቀይ ባሕርና የአደን ባህረ-ሠላጤ አካባቢ መንግስታትን የሚያሰጋ አይምስልም።

«እስካሁን በቀይ ባሕር አዋሳኝ ሐገሮች በተለይ በቅርብ ያሉት ጅቡቲና ሶማሊያን በመሳሰሉ ሐገራት ላይ ያን ያሕል ተፅዕኖ አይታይም።ጅቡቲ ዉስጥ ያሉ የምዕራባዉያን ወታደራዊ ሠፈሮችን የየመን ሁቲዎች እንዳያጠቁ፣ የምዕራባዉያን ጦርም ከዚያ ተነስቲ ሁቲዎችን እንዳጠቃ የሆነ የዉስጥ ሥምምነት ያለ ይመስላል።አሜሪካኖችንም ጥንቃቄ እያደረጉ ነዉ።»

በ2024 መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ወደብ ለመኮናተር  የመግባቢያ ስምምነት ሥትፈራረም፣ የግብፅ ገዢዎች ለ33 ዓመታት የዘነጉትን የሶማሊያ ጉዳይ ዶሴን አዋራዉን አራግፈዉ ገልጠዉታል፤ ከሞቃዲሾ መሪዎች ጋር «ሥልታዊ» ያሉትን ወዳጅነት መሠረተዋልም።ከአሥመራ ገዢዎችም ጋር ነባር ወዳጅነታቸዉን አድሰዋል።

ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድና የቀድሞዉ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የመግባቢያ ስምምነት ሲፈራረሙ
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድና የቀድሞዉ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የመግባቢያ ስምምነት ሲፈራረሙምስል፦ TIKSA NEGERI/REUTERS

ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አልሲሲ ሐገራቸዉ ድንበር ጋዛ ዉስጥ የሚደርሰዉ እልቂት፣የቀይ ባሕር ጥቃት፣የየመን መደብደብ፣ የሱዳንና የሊቢያ ትርምስ ያሳስባቸዉ ይሆናል።ሰሞኑን በጣም ያሳሰባቸዉ ግን ከሶማሊያ ፕሬዝደት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ጋር አምና ነሐሴ የተፈራረሙት ሥልታዊ ወዳጅነት ነዉ።ምክንያቱ ደግሞ ታዛቢዎች እንዳሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ አዲስ አበባ ላይ የሰጡት መግለጫ ሳይሆን አይቀርም።

«ለግብፅ መንግሥት፣ ለሱዳን መንግስት እንዲሁም ለተፋሰሱ ሐገራት በሙሉ መስከረም፣ ዝናብ ጋብ ሲል፣ ሕዳሴን ሥናስመርቅ የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ በተከበረዉ ምክር ቤት ፊት ግብዣ አቀርብላቸዋለሁ።»

አል ሲሲ ምናልባት አዲስበባና በኒ ሻንጉል-ጉሙዝን እንዲጎበኙ ከአዲስ አበባ በተጋበዙ በ4ኛዉ ቀን የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድን ጋበዙ።ይሕም ሐምሌ 7 ነበር።የሶማሊያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ የግብፅና የሶማሊያ መሪዎች አዲስ በተገነባዉ አል-አላማይን ቤተ መንግሥት ዉስጥ ያደረጉት ዉይይት የሶማሊያና የአካባቢዉን ፀጥታና ሠላምን ለማሥረፅ ሁለቱ ሐገራት በጋራ የሚያደርጉትን ጥረት ለማጠናከር ያለመ ነዉ።

ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት ግን የአል-ሲሲና  የሼኽ ማሕሙድ ዉይይት የሕዳሴ ግንድብ ግንባታና ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነትን በቀጥታ እንደሚመለከት ለተንታኞች የተሰወረ አይደለም።

«ምንም እንኳን መንግሥታት የሚሰጡት መግለጫና እነሱ የሚያቀርቡት ገፅታ ለቀጠናዉ ሠላም ነዉ።ከፀረ አ,ሸባሪዎች ኃይላት ጋር ነዉ የተነጋገርነዉ፣ ለኢኮኖሚ  ነዉ ሊሉት ይችላሉ።ጠ,ቅላይ ሚንስትር ዐብይ እሚወስዷቸዉን እንቅስቃሴዎች፣ የሚያቀርቧቸዉን አጀንዳዎች፣ የሚያደርጓቸዉ ንግግሮች ሶማሊያ የምታደርገዉን የዉጪ ጉዳይ ግንኙነትን እየወሰ ነዉ።»

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድና የቀድሞዉ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሕ አብዲ ጥር 2024 የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሙሉ በሙሉ መሠረዝ-አለመሰረዙ አይታወቅም።በሥምምነቱ ምክንያት የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ መንግስታት የገጠሙት ጠብ በቱርክ ሸምጋይነት የረገበ መስሏል።ጠብ-ቅሬታዉ ሙሉ በሙሉ አልተወገደም።

የሞቃዲሾ-ግብፅ-አሥመራ ገዢዎች የጋራ ግንባር

ስምምነቱን በመቃወም የሞቃዲሾ፣ ካይሮ አሥመራ ገዢዎች የመሠረቱት ፀረ-አዲስ አበባ ትብብርም እየተጠናከረ ነዉ።ኢትዮጵያ እንደተባለዉ መስከረም ላይ የሕዳሴ ግድብን ከማስረቋ በፊት ነሐሴ ላይ አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት አብዱረሕማን መሐመድ ኢሮ አዲስ አበባን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉብኝቱ «በጠወለገዉ» የመግባቢያ ስምምነት ላይ ነብስ ከዘረባት እስካሁን ገሚስ የህወሓት መሪዎችን የክበቡ አካል ለማድረግ የሚዉተረተረዉ የሞቃዲሾ፣ ካይሮ፣ አሥመራ ገዢዎች አክሲስ ወይም ሥብስብ ምናልባት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) ገሚስ መሪዎችን ሊያቅፍ፣ አጓጉል መዘዙ ከትግራይ እስከ ኦጋዴን ሊደርስ ይችላል።

ከህወሓትና ከትግራይ ኃይላት መሪዎች መካከል ገሚሶቹ ከአሥመራ ገዢዎች በተዘዋዋሪም ከካይሮና ከሞቃዲሾ ገዢዎች ጋር እንዳዲስ ለወዳጅት አንዴ የሕዝብ-ለሕዝብ ሌላ ጊዜ፣ የንግድ ደግሞ ሌላ ጊዜ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አቀንቃኝ በሚባሉ ደጋፊዎቻቸዉ በኩል ዙሪያ ጥምጥም እየተሽከረከሩ ነዉ።

ሌሎቹ የቀድሞ የህወሓት ፖለቲከኞችና የጦር አዛዦች ባንፃሩ ከአዲስ አበባ መንግሥት ጋር ማበራቸዉ እየተነገረ-አንዳዴም በግልፅ እየታየ ነዉ።ግራ- ቀኝ የቆሙት የህወሓት ፖለቲከኞች ከዘላቂ ሥልት ወይም ከስትራቴጂ ይልቅ በጊዚያዊ ታክቲክ ላይ ያነጣጠረዉ የተቃራኒ ኃይላትን የመወዳጀት ብልሐት ያን ከጦርነት ያላገገመ ክልልን የመቀሌዉ ነዋሪ እንዳለዉ ከዳግም ጦርነት እንዳይሞጅረዉ ነዋሪዎችን እያሰጋ ነዉ።

ሰነዓ።እስራኤልን የሚደግፈዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የመን ላይ በከፈተዉ ጥቃት ከተገደሉ የየመን ዜጎች የከፊሉ የቀብር ሥርዓት።ሚያዚያ፣ 2025 (እግአ)
ሰነዓ።እስራኤልን የሚደግፈዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የመን ላይ በከፈተዉ ጥቃት ከተገደሉ የየመን ዜጎች የከፊሉ የቀብር ሥርዓት።ሚያዚያ፣ 2025 (እግአ)ምስል፦ Khaled Abdullah/REUTERS

«ሰዉ ከባንክ ብር  እያወጣ ነዉ።ጤፍ እየገዛ፣ ዘይት እየገዛ የሌለ ክራይስስ ነዉ ያለዉ።እነዚሕ ጊዚያዊ አስተዳደር የሚባሉ፣ የእነዚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህወሓት የሚባሉ አባላት ወይ ሥልጣናቸዉን መልቀቅ ወይ ሥልጣናቸዉን በአግባቡ ተጠቅመዉ—»

የሠላም ሽምግልና የተስፋ ቃላት ዋጋ አላቸዉ ይሆን?

የትግራይ ክልል የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ተወካዮችም ጦርነት እንዳይጫር ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር ለመነጋገር ባለፈዉ ቅዳሜ አዲስ አበባ ገብተዋል።እርግጥ ነዉ የኃይማኖት መሪዎቹ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ላሰሙት ማሳሰቢያ ፈጣን መልስ ሰጥተዋል።ይሁንና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸዉን ልዩነት ያልፈቱት ወይም መፍታት ያልቻሉት የትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች ሽምግልና ሥጋቱን ማስወገድ መቻሉ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነዉ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የኃይማኖት መሪዎችንና ሌሎች ወገኖችን ባሳሰቡበት መልዕክታቸዉ መንግሥታቸዉ ትግራይ ዉስጥ ዉጊያ እንደማይከፍት ተናግረዋልም።

«ባለሐብቶች፣ ሙሕራን፣ ኤምባሲዎች አሁን ዉጊያ እንዳይጀመር ሚናችሁን ተወጡ።ምክንያቱም ከተጀመረ ከዚሕ በፊት የምናዉቀዉ ዓይደለም ይበላሻል ነገር።በኛ በኩል በትግራይ ምድር አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም።»

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጄኔራል ታደሰ ወረደም በትግራይ ክልል በኩል ዉጊያ አይጀመርም ብለዋል።

«በየትኛዉም መንገድ ቢሆን በትግራይ ክልል በኩል የሚጀመር ጦርነት ወይም ትንኮሳ አይኖርም።ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎቱም ዕቅዱም የለንም።ምክንያቱም ለሰላም አሁንም ዕድሉ አለ የሚል ፅኑዕ እምነት ሥላለን።»

ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ፣ የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶሐንና የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ።ታሕሳስ 2024 (እግአ) ኢትዮጵያና ሶማሊያ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ፣ የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶሐንና የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ።ታሕሳስ 2024 (እግአ) ኢትዮጵያና ሶማሊያ የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙምስል፦ DHA

የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት በመላዉ የአፍሪቃ ቀንድ መሪዎች ወይም ፖለቲከኞች ዘንድ መተማመን የለም።የመተማመኑ እጦት የአንድ ሐገር መሪ ወይም ፖለቲከኛ የሚል-የሚያደርገዉን የሌላዉ ሐገር መሪ፣ አጠቃላይ ሕዝቡም እንዲጠራጠር አድርጎታል።

የቀድሞዉ የሶቭየት ሕብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን ባንድ ወቅት «የአንድ ሐገር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሰላም ጉባኤ እንዲደረግ እስከመጨረሻዉ ድረስ እታገላለሁ ካለ» አሉ-አሉ ፀሐፊዎች-«የዚያች ሐገር መከላከያ ሚንስትር ለዉጊያ እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠርጥር» አከሉ።