በአፋር ክልል ካሉ ታጣቂዎች ወደ ትግራይ ክልል ማንኛውም ትንኮሳ የሚመጣ ከሆነ ተጠያቂው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ገለፁ። በአፋር ካሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ታጣቂዎች ጋር ያለው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ያሉት ፕሬዝደንቱ፥ ይሁንና የውክልና ግጭት ለመፍጠር ከተሞከረ ግን ጉዳዮ ከፌደራል መንግስት ጋር ነው የሚሆነው ሲሉ ጀነራል ታደሰ ወረደ አስታውቀዋል። ህወሓትም በበኩሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አውጥቶት በነበረ መግለጫ የፌደራሉ መንግስት ታጣቂዎች እያሰባሰበ እና እያስታጠቀ ነው ሲል ከሷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጥሪ
ትላንት በመቐለ ሓወልቲ ሰማእታት አደራሽ በነበረ የትግራይ ሰማእታት መታሰብያ መዝግያ ስነስርዓት ንግግር ያሰሙት የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በክልሉ ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ከህወሓት ክፍፍል በኃላ የተለየ ፖለቲካዊ አቋም በመያዝ ከነባር የትግራይ ሐይሎች በመለየት በአፋር ክልል እየተደራጁ የቆዩት ታጣቂዎች ጉዳይ በዝርዝር ያነሱት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ከእነዚህ ታጣቂዎች በኩል የሚደረግ ማነኛውም ትንኮሳ ግዚያዊ አስተዳደሩ ጉዳዩ የእነሱ አድርጎ ሳይሆን የፌደራሉ መንግስት ትንኮሳ አድርጎ እንደሚያየው ገልፀዋል።
በትግራይ የግብርና ምርት በግብአቶች እጥረት ተመናምኗል ተባለ
ጀነራል ታደሰ “በእዛ አቅጣጫ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ትንኮሳ እንደ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ጉዳዮ እዛ ያሉት [ታጣቂዎች] አድርጎ አይወስደውም። ወይም የፌደራል መንግስት ነው፣ አልያም የአፋር ነው። እዛ ካሉት [ታጣቂዎች] ጋር ያለው ነገር በሰላም መፈታት አለበት። የሆነ ይሁን ትንኮሳ ግን ከአፋር አቅጣጫ ከመጣ የአፋር ወይም የፌደራል መንግስት ነው እንጂ የተጋሩ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ኤሬፒቲ ወይም ሽኸት ያሉ [ታጣቂዎች] ስላደረጉት ከእነሱ ጋር የሚደረግ ድርድር ይሁን ንግግር የለም፥ ይህ ሲከሰት ተጠያቂ የሚሆነው የፌደራሉ መንግስት ነው። ከአፋር ክልል ጋር ደግሞ በተቻለ መጠን ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሆን ይደረጋል። ከትንኮሳዎች ጋር በተያያዘ ግን የፌደራል መንግስት ሐላፊነት አለው” ብለዋል።

“በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት የጦርነት ፍላጎትም ሆነ ዝግጅት የለም” – ህወሓት
በአሁኑ ወቅት ‘ውጥረቶች’ መኖራቸው ያነሱት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጄነራል ታደሰ ወረደ፥ ይህ የሚያባብሱ ያላቸው መንገድ መዝጋት፣ ግብአቶች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ መከልከል የመሳሰሉ ተግባራት አደገኛ እና ሊከሰቱ የማይገቡ መሆናቸው አብራርተዋል። ከህወሓት ክፍፍል በኃላ ማእከላቸው አፋር ያደረጉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ታጣቂዎች ለወራት ሲደረጁ ከቆዩ በኃላ በቅርቡ ወደ ትግራይ አቅጣጫ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስለማድረጋቸው መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፥ ከእነዚህ ታጣቂዎች ጋር ያለው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚሰራም ፕሬዝደንቱ ጨምረው ገልፀዋል።
የምክክር ኮሚሽን ሥራውን በትግራይ ክልል እንዴት እያካሄደ ነው?
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በንግግራቸው “[ታጣቂዎቹ] የውክልና ሐይል እንዳይሆኑ ሁሉም የሚቻለው ነገር ይደረጋል። የውክልና ሐይል ሆነህ የምታደርገው እንቅስቃሴ የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ስለሆነ የሚፈታበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ለዚህ ደግሞ ሐላፊነቱ የኛ ይሆናል” ሲሉ ገልፀዋል።ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መግለጫ አውጥቶ የነበረው ህወሓት የፌደራሉ መንግስት ትግራይን ለማጥቃት ታጣቂዎች እያሰባሰበ እና እያስታጠቀ ነው ብሎ ከሷል። በእነዚህ ህወሓት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሚያነሷቸው ጉዳዮች ዙርያ ከፌደራል መንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። https://www.dw.com/am/