በጀኔቫ የተመድ ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው፣ አምባሳደር ጸጋአብ፣ የኤርትራ ድርጊት በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ የጦርነት ስጋት የሚደቅን ነው በማለት ከሰዋል። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኤርትራ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ልዩ ራፖርተር የጊዜ ቆይታን ለማራዘም ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በተሰበሰበበት ወቅት፣ አምባሳደር ጸጋአብ የኤርትራ ወታደሮች በተቆጣጠሯቸው የትግራይ አካባቢዎች የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እየፈጸሙ ይገኛሉ ብለዋል። አምባሳደሩ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ደቅነዋለች ላሉት ስጋት፣ የኤርትራ ወታደሮች የትግራይ አንዳንድ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ የተመድ ልዩ ራፖርተር ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን ሪፖርት በአስረጅነት ጠቅሰዋል።
በተመድ የጀኔቫ ቋሚ ጽሕፈት ቤት የኤርትራ ልዑክ ሃብቶም ዘርዓይ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ውንጀላ ካለፉት ድርጊቶቿና አቋሞቿ ጋር የማቃረንና ወጥነት የሌለው መኾኑን በመጥቀስ በምክር ቤቱ ውስጥ ምላሽ ሠጥተዋል። የኤርትራ ጦር በዓለማቀፍ ሕግ በሚታወቀው የኤርትራ ግዛት ብቻ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሃብቶም፣ የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ግዛቶች ይዟል የሚባለው ትርክት “ጦርነት ለመቀስቀስ” እና “ለጦርነት ሽፋን ለመፍጠር ያለመ ሴራ” ነው በማለት ውድቅ አድርገውታል። ኢትዮጵያ ባኹኑ ወቅት በይፋ ዛቻዎችን መሠንዘር፣ ጦር መሳሪያ ማከማቸትና ቀጠናዊ ሰላምና ጸጥታን የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን መፈጸም ቀጥላለች ያሉት ሃብቶም፣ ኢትዮጵያ ይህን የምታደርገው ውስጣዊ ችግሮቿን ለመሸፋፈን መኾኑን ምክር ቤቱ መረዳት አለበት ብለዋል።