የሕዳሴ ግድብ በግብጽ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኢትዮጵያ ዋጋ ትከፍልበታለች

የግብጽ የመስኖ ሚንስትር ሃኒ ስዊላም፣ የሕዳሴ ግድብ በግብጽ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኢትዮጵያ ዋጋ ትከፍልበታለች በማለት ማስጠንቀቃቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ሚንስትሩ፣ ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ ያላት ጥቅም ከተነካባት፣ አስፈላጊ የኾኑ ርምጃዎችን ትወስዳለች በማለት እንደዛቱ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።

ሚንስትሩ፣ በድርቅ ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት እንዲኹም በግድቡ ውሃ አሞላል ሂደት እና በውሃ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ተብሏል።

የሦስቱ አገራት የመርኾዎች ስምምነት፣ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት ያደረሰ አገር የጉዳት ማካካሻ እንዲከፍል ያስገድዳል ማለታቸውን የጠቀሱት ዘገባዎቹ፣ እስካኹን ባለው የድርድሩ ቅርጽ ሌላ ዙር ድርድር ማድረግ ጊዜ ማባከን እንደኾነም መናገራቸውን አመልክተዋል።