የመሀል ሜዳው ተጫዋች አለልኝ አዘነ ለህልፈት መዳረጉን ተከትሎ ወንድም እና እህቱን በቁጥጥር ስር አድርገን ምርመራ እያካሄድን ነው

” ወንድም እና እህቱን በቁጥጥር ስር አድርገን ምርመራ እያካሄድን ነው ” – የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የባህር ዳር ከተማ የመሀል ሜዳው ተጫዋች አለልኝ አዘነ ለህልፈት መዳረጉን ተከትሎ ቤተሰቦቹ  በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሰምቷል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጠው ቃል ፥ ” አሟሟቱ ድንገተኛና አሰቃቂ መሆኑን ተከትሎ የቅርብ ግንኙነት ያላቸዉን አካላት ይዤ ምርመራ ጀምሪያለሁ ” ብሏል።

የወጣቱ ህይዎት ይቀጠፍ ዘንድ ምክኒያት የሆኑ ጉዳዮችን ለማወቅ የስልክ ልውውጦችን ከመመርመር በተጨማሪ በዙሪያው የነበሩ አካላትንም በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገልጿል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እነማን ተያዙ ? የምርመራዉ አካሄድስ ምን ይመስላል ? ሲል ለአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የለሆኑት ኢንስፔክተር አብርሀም ሙሄ ጥያቄ አቅርቧል።

” የተጫዋቹ መሞት በተሰማበት ወቅት አጠራጣሪ ጉዳዮች ስለነበሩ ፖሊስ የምርመራ እንቅስቃሴ ጀምሯል ” ያሉት ኢንስፔክተር አብርሀም ” በዚህ ወቅት ወንድም እና እህቱን በቁጥጥር ስር አድርገን ምርመራ እያካሄድን ነው ” ብለዋል።

በሶሻል ሚዲያ እየተዘዋወረ ያለዉን የእናቱ እና ባለቤቱ መያዝ በተመለከተ ላነሳንላቸዉ ጥያቄ ” አሁን ላይ ከእህት እና ወንድሙ ዉጭ የተያዘ አካል የለም በማለት ወደፊት ግን ከተያዙት የሚለቀቅ ካልተያዙት ደግሞ የሚያዝ ሊኖር ይችላል ” ብለዋል።

” አሁን ላይ ምርመራዉን በፍጥነትና በጥንቃቄ እያካሄድን ነው ” ያሉት ኢንስፔክተር አብርሀም ሙሄ ውጤቱን ለመላ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማድረስ ማሰባቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ጠቁመዋል።