የጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄረተኝነት የጀርባ አጥንት የሚሰበረው በሸዋ ኦሮሞዎች ነው #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

አንዳንድ ወገኖች ስለኦሮሚያ ክልል ለምን ብዙ ትጽፋለህ ይላሉ። ምክንያቱ ቀላል ነው፤ በአገራችን ካሉት ችግሮች ዋናዎቹ ያሉት በኦሮሞ ክልል በመሆኑና በኦሮሞ ክልል ያለው መረን የለቀቀ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄረተኝኘት ትልቁ የአገራችን ፈታና ስለሆነ ነው።

አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ስለ ሸዋ ስጽፍ ሸዋዬ አድርገው ይወስዱኛል። ለነገሩ ሸዋዬ ነኝ።የሸዋ ሰው።ሸገር፣ አዲስ አበባ የሸዋ እንብርት ናት። ስለዚህ እንደ ሸገር ልጅ የሸዋ ልጅም ነኝ። ሸዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ እንደመሆኑም ኢጆሌ ሸገር፣ ኢጆሌ ሸዋ ፣ ኢጆሌ ኢትዮጵያ ነኝ።

የተወለድኩትና ያደኩት አዲስ አበባ ሸዋ ነው። አያት ቅድም አያቶቼ ከሸዋ ነበሩ። ሁለት ከአዳ(ቢሾፍቱ አካባቢ)፣ አንድ ከሸንኮራ፣ አንድ ከመንዝ። ሁለት ወደ ነገሌ ቦረና ሁለት ደግሞ ወደ ጎጃም ናቸው። ስለዚህ ሸዋ በመወለዴና ግማሽ የሚሆኑ ቅድም አያቶቼ ከሸዋ ስለነበሩ፣ ከሸዋ ጋር አዎን የበለጠ ቁርኝነት አለኝ።

ግን ስለ ሸዋ የምጽፈው እኔ ከሸዋ ጋር የበለጠ ቁርኝነት ስላለኝ አይደለም። የኢትዮጵያ አንድነት ማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያዊነት ማስቀጠል የሚቻለው ሕብረብሄራዊ የሆነችዋን ሸዋን እንደገና በማጠናከር ነው።

ሸዋን እንደገና ማጠናከር በጣም እጅግ ሲበዛ በጣም ቀላል ነው። የሸዋ ሕዝብ፣ በያንዳንዱ ወረዳ አስተያየቱን እንዲጠይቅ ማድረግ ነው። “በኦሮሞ ክልል መቀጠል ትፈልጋላችሁ ወይስ አማርኛና ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ተደርጎ ሸዋ የራሱ ፈዴራል መስተዳደር ሆኖ እንዲቀጥል ትፈልጋላችሁ ?” በሚል ህዝብ ቢጠየቅ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሸዋን መስተዳደር መመለስ የሚፈልጉ አብላጫ ድምጽ ሊኖራቸው ይችላል ብዬ አስባለሁ።

አንደኛ – በሸዋ በተለያዩ ቦታዎች በሃላፊነት የተቀመጡት ከወለጋ፣ አርሲ …የመጡ ናቸው። የሸዋ ኦሮሞዎች ራሳቸው፣ በሸዋ፣ በሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች የተገለሉበት ሁኔታ እንዳለ ነው የሚነገረው። የሸዋ ኦሮሞዎች በብዛት ከአማራ ከጉራጌ..ጋር የተዋለዱ ናቸው። እንደ ኦሮሞም አይቆጥሯቸውም። “አማራ” ነው የሚሏቸው። ለምሳሌ በአርሲ ከሸዋ የሄዱ በርካታ ኦሮሞዎች አሉ። በኦሮሞዎች ልዩነት የሚደረግባቸው።የሚገፉ። ወደ ስልጣን እንዲመጡም የማይፈለጉ።ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የሸዋ ኦሮሞ የአርሲ፣ ወለጋና ጅማ ያሉ የኦሮሞ ብሄረተኞች ስር ከመገዛት ውጭ ምንም አላተረፈም። ላለፉት 27 አመታት የኦሮምያ ርዕሠ መሥተዳደር አልያም ምክትል ርዕሠ መሥተዳደር የነበረ የሸዋ ሠው አይገኝም። ምክንያቱም አያምኗቸውም። ዶ/ር መራራ ጉዲና የህይወት ታሪካቸውን በዳሰሡበት መጽሐፍ “አርሲና ወለጋወች ባገኟቸው ቁጥር አንተ ነፍጠኛ በማለት ለሠላምታ እንደሚጸየፏቸው ተርከውልናል

ሁለተኛ – የሸዋ ኦሮሞዎች፣ በጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ የችግሩ አካል ተደርገው ነው የሚታዩት። ጎበናዎች ነው የሚባሉት። እነ አቡነ ጰጥሮስ (አባ መገርሳ)፣ እነ ባልቻ አባ ነፍስ፣ እነ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ፣ እነ ፌታውራሪ ሃብቴ ዲነግዴ፣ ቁጥር የለሽ የኦሮሞ ጀግኖችን ሸዋ አፍርታለች። ግን የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄረተኞች፣ ከኦሮሞ ማህበረሰብ አልፈው ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ ገድል የሰሩ ታላላቅ ጀግኖችን የሚያሳንሱ ናቸው። እነርሱ ጀግና አድርገው የሚቆጥሩት ከሲያድ ባሬ ጋር ሆነው ሲዶልቱ የነበሩ እንደ ዋቆ ጉቱ ያሉትን ከሃዲዎችን ነው።

ሶስተኛ- በሸዋ እጅግ በጣም ብዙ የተደባለቀ ማህበረሰብ ነው ያለው። በመጋቢት ይደረጋል የተባለው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ፍትሃዊ፣ ነጻና ግልጽነት ባለው መልኩ ከተደረገ፣ በሸዋ አዲስ አበባን ጨምሮ ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ሕብረብሄራዊ መሆኑን እንደሚገልጽ ነው የሚጠበቀው። ሕዝቡ አብዛኛው ሕብረብሄራዊ በሆነበት ደግሞ የኦሮሞዎች ብቻ ተደርጋ በሕወሃትና በኦነግ በተጠፈጠፈች ክልል ውስጥ ይቀጥላል ብሎ ማሰብ አይቻልም።

አራተኛ – የሸዋ ኦሮሞ በባህል በሃይማኖት ለሸዋ አማራ እንጅ ያቤሎና ደምቢዶሎ፣ ጉሊሶና ጫርሶ ላሉ የቀረበ አይደለም።

ለዚህም ነው የኦሮሞ ብሄረተኞች ፣ በሸዋ፣ ህዝብ በያንዳንዱ ወረዳ ፍላጎቱ ይጠየቅ ሲባሉ ፍቃደኛ የማይሆኑት። እመኑኝ የአክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኝነት የጀርባ አጥንት የሚሰባበረው በማንም አይደለም በሸዋ ኦሮሞዎችና በሸዋ ህዝብ ነው።

የሸዋ መጠናከር ራሱን የቻለ የፌዴራል መስተዳደር መሆን፣ የኦሮሞ ብሄረተኞች የኦሮሞ ሪፑብሊክ የመመስረት ቅዠታቸውን ማበላሸት ብቻ አይደለም ሙሉ ለሙሉ ይደመስሰዋል።፡ያለ ሸዋ ኦሮሚያ ሪፑብሊክ የምትባል ነገር መቼም አትኖርም። ስለዚህ የሸዋን ሃይል በመበታተን፣ ጎበናዎች ናቸው የሚሏቸውን የሸዋ ኦሮሞዎች በማግለልና በማዳከም አሁን ያለው የዘር አከላለል እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት።

በመጨረሻ አንድ ነገር ላይ በትልቁ ላስምረበት። ሸዋ ሰል አማራ ማለቴ አይደለም። ሸዋ ስል አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ..በሸዋ የሚኖር ሁሉም ሕዝብ ማለቴ ነው። ሸዋ ስል አማርኛ ብቻ ማለቴ አይደለም። ኦሮምኛም፣ ጉራጌኛውም ..በሸዋ የሚነገሩ ቋንቋዎችንም ማለቴ ነው።

ከኦሮሞ ጋር ጠብ የለኝም። ኦሮሞ አያት ቅድም አያቶች አሉኝ። ከኦሮምኛ ጋር ጠብ የለኝም። የአያቶቼን ቋንቋ ባውቅና ብማር ደስ ይለኛል። ጠቤ ግን ለዘመናት አብሮን የኖረን፣ ታሪክን የሰራን የሸዋ ማህበረሰብ አማራ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ ተብሎ እንዲከፋፈል መደረጉ ነው።