ኦሮሞ ኤጲስ ቆጶሳትን ምልመላና ምርጫ የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጧል

የዘጠኙ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሥርዓተ ሢመት ሐምሌ 9/2015 እንደሚከናወን ተገለጸ

👉የኤጲስ ቆጶሳቱን ምልመላና ምርጫ የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጧል

በኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመረጡ ዘጠኝ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሥርዓተ ሢመት ሐምሌ 9/2015 እንደሚከናወን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስታወቀ።

ምልዓተ ጉባኤው የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምልመላና ምርጫ የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ መምረጡን አስታውቋል።

የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው አጀንዳዎች መካከል የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና ሢመት አንዱና ዋነኛው ነው።

በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጉዳዩ ዙሪያ ለሦስት ቀናት ከተወያየ በኋላ፤ ለአሁኑ ችግር ባላባቸውና አስፈላጊ በሆነባቸው ዘጠኝ አህጉረ ስብከት ላይ በዚህ ዓመት 2015 ዘጠኝ አዳዲስ ኤጲስ ቆጳሳት እንዲሾሙ ብሏል፡፡ እንዲሁም በጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን እውነትና ቀኖናን እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ባደረገ መልኩ ብሎም አባቶች በሚያስፈልጉባቸው አህጉረ ስብከት የአዳዲስ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ጉዳይን እንደሚመለከተው ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም መሠረት በዚህ ዓመት በሚካሄደው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙ አባቶች የሚመደቡባቸው የ(9)ኙ አህጉረ ስብከት ሥም ዝርዝር

1. ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት

2. ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት

3. ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት

4. የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት

5. ምዕራብ አርሲ (ሻሸመኔ) ሀገረ ስብከት

6. ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት

7. ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት

8. ጌዴኦ ቡርጅና አማሮ ሀገረ ስብከት

9. ዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት መሆናቸው ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ምልዓተ ጉባኤው ይህን ጉዳይ በጥናትና በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት የሚለይና የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት የተካተቱበት አስመራጭ ኮሚቴ መምረጡም ተገልጿል።

የአስመራጭ ኮሚቴው አባላትም ሥም ዝርዝርም

1) ብፁዕ አቡነ ሄኖክ

2) ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

3) ብፁዕ አቡነ ማርቆስ

4) ብፀዕ አቡነ ናትናኤል

5) ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ

6) ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

7) ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በመሆን ኮሚቴው መዋቀሩ ተነግሯል።

አስመራጭ ኮሚቴው ጥናቱንና ምልምላውን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር በመናበብ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት በማድረግ ለመጨረሻ ምርጫ ለምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው እንደሥርዓቱ በመምረጥ 9ኙን መነኮሳት እንደሚለይ አስታውቋል።

በምልዓተ ጉባኤው የተመረጡ 9ኙ መነኮሳት አባቶች ሥርዓተ ሢመት ሐምሌ 9/2015 በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ ዕድ እንደሚፈጸም ከተዋህዶ ሚድያ ማዕከል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
____